አፍሪካ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ቢኖራትም ሀብቱን ለልማት አውሎ የዜጎችን ሕይወት መቀየር፤ አህጉሪቱንም ከድህነት ማውጣት ግን አለመቻሉን የአህጉሪቱን ጉዳይን በቅርበት የሚከታተሉ እና የሚተነትኑ ባለሙያዎች የሚገልጹት እውነታ ነው፡፡
የአፍሪካ ጉዳይ ተመራማሪው ኬንያዊው የህግ ባለሙያ እና አክቲቪስት ፕሮፌሰር Patrick Loch Otieno Lumumba ከአንድ ዓመት በፊት ከናይጄሪያ ሌጎስ በቻናልስ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ ስርጭት በተላለፈ ንግግራቸው አፍሪካ በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሰች የተፈጥሮ ሀብቷ አላግባብ እየባከነ እንዳለ ገልጸዋል፡፡
ማሊ በእርስ በእርስ ግጭት ምክንያት መከፋፈሏን፤ በዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎም በርካታ ታጣቂዎች መሽገው እንደሚገኙ፤ ዜጎችን እንደሚያሸብሩ የአገሪቱም የተፈጥሮ ሀብት አላግባብ እንደሚበዘበዝ ተናግረዋል፡፡
ፕሮፌሰር ፓትሪስ ሉሙምባ በግጭት እና አለመረጋጋት ምክንያትም የዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ የተፈጥሮ ሀብት አላግባብ እንደሚባክን ነው የገለጹት፡፡ በሌሎችም የአህጉሩ አገራት ተመሳሳይ ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡
አፍሪካ በቀኝ ገዢዎቿ ቁጥጥር ስር እድትገባ ትኩረታቸውን የሳበው ይኸው የተፈጥሮ ሀብቷ እንሆነም ነው በርካቶች የሚገልጹት፡፡ ዛሬም ድረስ በአብዛኛው የአህጉሩ አገራት የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ሲውል፤ ኢኮኖሚን ሲያሳድግ፤ የዜጎችን ህይወት ሲቀይር አይስተዋልም፡፡ ከዚያ ይልቅ ሀብቱ የሃይል ስበት፤ የግጭት ማዕከል እንደሆነ ይመላከታል፡፡
አለም አቀፍ የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ የተፈጥሮ ሀብት በባህሪው የግጭት ምክንያት፤ ለቀውስም የሚያጋልጥ ነው ይላሉ፤ አገራት ወይም ግለሰብ ትከሻቸውን የሚለካኩበት አቅም ማሳያ በመሆኑ ግጭትን ይስባል፤ ለቀውስም ያጋልጣል ብለዋል፡፡
በምሳሌነት የጎረቤት አገር ሱዳንን ግጭት ይጠቅሳሉ፡፡
በኢትዮጵያም የተለያዩ የማዕድን ሀብቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዘርፍ ተሰማርተው ከሚገኙ የግል ድርጅቶች አንዱ ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ነው፡፡ በድርጅቱ ሲኒየር ጂኦፊሲስት አቶ ዘሪሁን ግርማ፤ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩብ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወርቅን ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናትን በማውጣት ለአለም ገበያ እያቀረበ እንዳለ ተናግረዋል፡፡ አይረን፤ ወርቅ፤ ቤንቶናይት፤ የድንጋይ ከሰል እና ሌሎችም ማዕድናት ዋነኞቹ የሚያወጣቸው ማዕድናት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሀብቱ በህገ-ወጥ መልኩ ከአገር እንዳይወጣ በቀጥታ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንደሚገባ ያስረዱት ባለሙያው፤ በማዕድን ማውጣት ዘርፍ ለሚሰማሩ ማህበራት እና ድርጅቶች መሰረታዊ ተግዳሮት የሚሆነው የጸጥታ ችግር እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
ሀብቱ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚገኝባቸው አከባቢዎች አንዱ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ነው፤ በክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደርበው ዘንቶ በክልሉ ከ1ሺ 200 በላይ ማህበራት ተደራጅተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ያሉ የማዕድን ሀብቶችን በሙሉ ለመጠቀም ሀብቱን የመለየቱ ስራ በበቂ እንዳልተሰራ ተናግረዋል፤ ከፍተኛ የወርቅ ማዕድን ያለበት ክልሉ ባለፉት ጊዜያት ህገወጥ የወርቅ ንግድ እና ዝውውር ተግዳሮት እንደነበር አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ወርቅ በብሔራዊ ባንክ እና በህገወጥ መልኩ የሚሸጥበት ዋጋ ከፍተኛ ልዩነት እንደነበረው ገልጸው፤ ይህም በመሆኑ በዘርፉ የተደራጁ አካላት ህገ-ወጥ ሽያጭን አማራጭ ሲያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል፡፡
ህገ-ወጥ የማዕድን ሀብት ስርጭትን ለመቆጣጠር በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ የማዕድን ግብይት ቁጥጥር ግብረ-ሃይል ተቃቁሞ እየሰራ እንዳለ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በአከባቢው የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር እና የመሰረተ ልማት እጥረት መቅረፍ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የአማራ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና የስነ-ምድር ተመራማሪው አቶ ዝናው አበበ በኢትዮጵያ ያሉ አጠቃላይ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከሚያመርቱት ግማሽ ያህል መጠኑ በክልሉ እንደሚመረት ገልጸዋል፡፡ የግራናይት ምርትም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚመረት የተናገሩት ባለሙያው በቅርቡ አዲስ ምርት መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡
በአማራ ክልል 10 ዩኒቨርስቲዎች እንዳሉ የተናገሩት አቶ ዝናው፤ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ በዘርፉ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ከማስመረቅም ባለፈ፤ በ2014 ዓ/ም ዩኒቨርስቲዎቹ የማዕድን ሀብቱ ላይ ጥናት እንዲያደርጉ የሚያስችል ስምምነት ተፈጽሞ በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አሁን በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር በቀጥታ ተቋሙን ባይመለከተውም፤ ዘርፉ ላይ ተግዳሮት ሊፈጥር እንደሚችል አመላክተዋል፡፡ በሌላ በኩል ህገ-ወጥ የማዕድን ሀብት ዝውውር ተግዳሮት መሆኑን እና ችግሩንም ለመቅረፍ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በትግራይ ክልል ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅ ማዕድን አላግባብ ከክልሉ እየወጣ እንዳለ ክልሉ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ሰምተናል፡፡ በተለይ ባለፉት ዓመታት በክልሉ የነበረው ጦርነት ሀብቱ አላግባብ እንዲባክን በህገወጥ መልኩ እንዲሸሽ ምክንያት መሆኑ ነው የተመላከተው፡፡
በትግራይ ክልል የመሬት እና ማዕድን ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ፍሰሀ ግርማይ፤ አሁንም ድረስ በክልሉ የማዕድን ሀብት በህገወጥ መልኩ ቢወጣም በአንጻራዊነት መሻሻል እንዳለ ተናግረዋል፤ ባለፈው ዓመት በህጋዊ መልኩ ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባ ወርቅ መጠን 3 ኪሎ ግራም ብቻ እንደነበር የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በተያዘው ዓመት 800 ኪሎ ግራም ገቢ ለማድረግ ታቅዶ ባለፉት 5 ወራት ብቻ 5ሺ100 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓል ብለዋል፡፡ አፈጻጸሙ የተሻሻለው መንግስት ጥብቅ ቁጥጥር ስላደረገበት ነው ሲሉ ገልጸወል፡፡
አፈጻጸሙ ከእቅዱ አንጻር ከፈተኛ ቢመስልም ካለው እምቅ ሀብት አንጻር ግን ውስን እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እስከታች ካሉ አደረጃጀቶች ጋር በመምከር ህገ-ወጦችን ወደ ህጋዊ መስመር የማስገባት ስራ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ሀብቱን በአግባቡ ማስተዳደር የሚያስችል ግልጽ መመሪያ እና ደንብ ወጥቶ እየተተገበረ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በጸጥታ በኩልም ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ እንዳለ ነው የገለጹት፡፡
ይሁን እንጅ በክልሉ የነበረው የጸጥታ ችግር አሁንም ድረስ የዘርፉ ተግዳሮት ሆኖ መቀጠሉን ገልጸው፤ ለአከባቢው ማህበረሰብ ብሎም በዘርፉ ለተሰማሩ ዜጎች ቀጣይነት ባለው መልኩ የድህረ ጦርነት የስነ-ልቦና ምክር አገልግሎት መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡
የስነ አመራር እና የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ አቶ ጌትዬ ትርፌ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎችም የአፍሪካ አገራት ማዕድን እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ባሉበት አከባቢ ግጭቶች እና ህገ-ወጥ ግብይት ይስተዋላል ብለዋል፡፡ ይህም የሆነው የተፈጥሮ ሀብት በባህሪው የግጭት መንስኤ ስለሚሆን፤ ታጣቂዎች የተፈጥሮ ሀብትን በመቆጣጠር ኃይል ለማፈርጠም ስለሚጠቀሙ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት ጠንካራ የአስተዳደር ስርዓትን መዘርጋት ችግሮቹን እንደሚቀርፍ ገልጸዋል፡፡
በተለይ በድንበር አቅራቢያ በበርካታ የአፍሪከ ሀገራት የተፈጥሮ ሀብቶች የግጭት መነሻ ሲሆኑ በህገወጥ መልኩ ሲሸሹ ይስተዋላል ይላሉ፡፡
የሌሎች አገራት ፍላጎት እና ጣልቃ ገብነት መኖርም በአገር ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ልማት ላይ እንዳይውል፤ የጸጥታ ችግር እንዲፈጥር በህገወጥ መልኩ ከአገር እንዲወጣ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ስለሆነም የተፈጥሮ ሀብት ጠንካራ የአስተዳደር ስርዓትን ይፈልጋል ባይ ናቸው፡፡
አለም አቀፍ የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ኢትዮጵያ የማዕድን ሀብት በአግባቡ የሚመራበት አዋጅ ቁጥር 816/2005 እንዳላት እና በዚህም ማዕድናት በትክክለኛው መስፈር ለአልሚዎች እንዲተላለፉ ወይም እንዲሰጡ፤ አልሚዎችም የአከባቢውን ማህበረሰብ በልማት ተጠቃሚ እንዲያደርጉ የሚያዝ የህግ ማዕቀፍ መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ይህንን የማስፈጸሙ ኃላፊነት ደግሞ የፌደራል የማዕድን ሚኒስቴር እና የክልል የማዕድን ቢሮዎች እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ እንደሌሎች ሀብቱ ያለባቸው አከባቢዎች በማእድን ሀብት የተነሳ ከፈተኛ ግጭት ባይኖርም አዝማሚያ እንዳለ የገለጹት ባለሙያው፤ በአገራችን የዘርፉ ከፍተኛ ችግር ህገ-ወጥ ሽያጭ እና ዝውውር ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ዘርፉ ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ እና የማስፈጸም አቅምን እንደሚፈልግ አስረድተዋል፡፡
በማዕድን ሚኒስቴር የማዕድን ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብስራት ከበደ በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ በማክሮ ኢኮኖሚክ ማሻሻያው ከ5ቱ የኢኮኖሚ ምሶሶዎች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዘርፈን ለአልሚዎች የማስተዋወቁ ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
እንደ ሀገር ያለውን የማዕድን ሀብት መጠን በሙሉ አጥንቶ ለማወቅ ሰፊ የአዋጪነት ጥናት እንደሚፈልግ፤ እሴት ጨምሮ መሸጥ ላይም ትኩረት እንደሚደረግበት ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራበት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ሀብቱ በስነ ምድር እና በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢንስቲትዩቱ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ጨምሮ በአፍሪካ እምቅ የማዕድን ሀብት ቢኖርም ሀብቱ አላግባብ እንዲባክን የግጭትም መንስኤ እንዲሆን ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ፤ የተቀናጀ የአፈጻጸም እና የሀብት አስተዳደር ውስንነት መኖሩ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
እንደ ሀገርም ከአምስቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምሰሶዎች መካከል አንዱ የሆነውን የማዕድን ሀብት ተጠቃሚነት ለማሳደግ፤ ህገ-ወጥ ግብይትን ለማስቀረት እንዲሁም የዘርፉን የግጭት የስዕበት ማዕከልነት ለማስወገድ ጠንካራ የማዕድን ሀብት አስተዳደር ስርዓት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ