♻️“በሃገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ውይይት ወቅት አስተርጓሚን ጨምሮ በብሬል የተዘጋጀ መረጃ የለም፤ መሰብሰቢያ አዳራሾቹና መጸዳጃ ቤቶቹ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አይደሉም”– አካል ጉዳተኞች
♻️“አናሳ የማህበረሰብ ክፍል ያላቸውን እና የተገለሉ ዜጎችን የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በትኩረት ሊያሳትፍ ይገባል፤አሳትፈናል ከማለት ባሻገር ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል ” –በኢትዮጵያ በሀገር በቀል እውቀቶች ላይ የሚመራመሩና በተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረታቸውን አድረገው የሚሰሩት ዶክተር አሉላ ፓንክረስት
♻️“አካል ጉዳተኞችን በምክክር ኮሚሽኑ ለማሳተፍ መሞከሩ የሚበረታታ ቢሆንም አሁንም ትኩረትን ይሻሉ፤እነሱም ብሶታቸውን መተንፈስ ይፈልጋሉና” – የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማሕበር
♻️“ታራሚዎችን እስካሁን አላሳተፍኩም፤ነገር ግን ተፈናቃዮችን ጨምሮ አካል ጉዳተኞችንና የተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማሳተፍ ጥረት እያደረግን ነው፤ አስተርጓሚን ጨምሮ በብሬል የተዘጋጀ መረጃ ለማቅረብም እየተሞከረ ነው፤ለቀጣይ በዚህ ጉዳይ ላይ አበክረን እንሰራለን” – የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ
✅በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነት እና አለመግባባት የሚታይ በመሆኑ ይህንን ልዩነትና አለመግባባት ለመፍታት ሰፋፊ ሃገራዊ የህዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠር ታስቦ የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ ይገለጻል።
የኮሚሽኑ አላማ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሰረታዊ በሆኑ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በመለየት እና ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት ምክክር እንዲደረግላቸው ማመቻቸት እንደሆነ ይገልጻል።
እንዲሁም የሚካሄድት ሃገራዊ ምክክሮች አካታች፤ብቃት ባለውና ገለልተኛ በሆነ አካል የሚመሩ፣ የአለመግባባት መንስኤዎችን በትክክል በሚዳስስ አጀንዳ የሚያተኩሩ እንዲሆኑ በማለም መሆኑ ይገለጻል።
የሚካሄዱት ሃገራዊ ምክክሮች በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እንዲሁም በመንግስት እና በህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል መተማመን የሰፈነበትና አዲስ የፖለቲካ ስርዓት መፍጠርን ጨምሮ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ለማዳበር እና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ምቹ መደላድል መፍጠርም የምክክር ኮሚሽኑ ዋና አላማ እንደሆነ ተመላክቷል።
ቢሆንም ግን በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል እየተፈጠረ ያለውን ግጭት በውይይት ለመፍታት አልሞ የተቋቋመ ቢሆንም አካታችነትን ተግባራዊ እያደረገ አይደለም በሚል በተደጋጋሚ ቅሬታ እየቀረበበት ነው፡፡
ኮሚሽኑ በሃገሪቱ የተለያዩ ክልሎች እየተዘዋወረ ውይይቶችን እያካሄደ ቢሆንም በማህበረሰቡ የተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን፤ አካል ጉዳተኞችን፤ተፈናቃዮችንና በእስር ላይ የሚገኙ ታራሚዎችን በሀገራዊ ምክክሩ በታሰበው ልክ እንዲሳተፉ እየሰራ ባለመሆኑ ተደጋጋሚ ቅሬታ እየተነሳበት ነው፡፡
ኮሚሽኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አናሳ የማህበረሰብ ክፍል ያላቸውን ማህበረሰቦችን ጨምሮ አካል ጉዳተኞችን ለማካተት ጥረት እያደረገ ቢሆንም አስተርጓሚን ጨምሮ በብሬል የተዘጋጀ መረጃ አለመኖሩን እና ውይይቶችን የሚያካሂድባቸው አዳራሾች እና መጸዳጃ ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ያልሆኑ መሆናቸውን በርካቶች በቅሬታ መልክ ሲገልጹ ይስተዋላል።
የሃገራዊ ምክክር ሂደቱ በብዛት እያሳተፋቸው አይደለም ከተባሉት የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል አካል ጉዳተኞችን፤ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ዜጎችን፤በግጭት ዉስጥ ያሉም ሆኑ ከግጭት እራሳቸዉን ያገለሉ አካላትን፤
ተፈናቃዮችን፤ ሴቶችን፤ ወጣቶችን፤ የዖታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎችን በማህበረሰቡ በኩል የተገለሉ በሚል የሚጠሩ ማህበረሰቦችን(ለአብነትም ሸክላ ሰሪ፤ጠንቋይ፣ ፋቂ፣ቡዳ፣ሃመር በሚል የሚጠሩ ጎሳዎችን) በብዛት እያሳተፉ እንዳልሆነ ትችቶች እየቀረቡለት ነው።
እኛም ይህንን ቅሬታ መነሻ በማድረግ የምክክር ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም የአጀንዳ ማሰባሰብ ካደረገባቸው እና በአሁኑ ወቅት ውይይት እያደረገ ከሚገኝባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ፤የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እንዲሁም በኦሮሚያ ክልሎች ተዘዋውረን ተሳታፊዎቹን ጨምሮ የአካባቢውን ማህበረሰብ ያነጋገርን ሲሆን የምክክር ኮሚሽኑ ውይይት የሚያደርግባቸው ቦታዎች በተለይ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆናቸውን ነግረውናል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም የምክክር ኮሚሽን ተሳታፊዎችን ጨምሮ በዘርፉ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋገረናል።
በኦሮሚያ ክልል አርሲ ጢዮ ከተባለ አካባቢ የአካል ጉዳተኞችን ሃሳብ ይዞ በምክክር ኮሚሽኑ ለመሳተፍ ወደ ቦታው ያቀናው አቶ ሞሃመድ ጃርሶ እንደሚገልጽት፤ የምክክር ኮሚሽኑ አካል ጉዳተኞችን ለማካተት ጥረት እያደረገ ቢሆንም “መስማት ለማይችሉ፤ግን ደግሞ ማየት ለሚችሉ አካል ጉዳተኞች አስተርጓሚ አልቀረበልንም” ብለዋል።
እንዲሁም “መስማትም ማየትም ለማይችሉ አካል ጉዳተኞች በብሬል የተዘጋጀ መረጃ ባለመኖሩ እነዚህን መሰል የማህበረሰብ ክፍሎችን ወክለው የመጡ አካል ጉዳተኞች ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ ሳይችሉ ቀርተዋል” ነው ያሉት። አክለውም፤የምግብ አማራጭ ለማዘዝ እንኳ አስተርጓሚ ባለመኖሩ እና በብሬል የተዘጋጀ የምግብ ዝርዝር እንዲሁም የውይይት አጀንዳ ባለመኖሩ ለችግር መጋለጣቸውን ነው የተናገሩት።
አቶ ሞሃመድ ጃርሶ አክለውም፤የምክክር ኮሚሽኑ አካታችነት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሊሰራ እንደሚገባው ጠቁመው፤በተሳታፊ ልየታ ወቅት አናሳ የማህበረሰብ ክፍል ያላቸውን ማህበረሰቦችም በትክክል ተካታች መሆናቸውን መፈተሽ እንዳለበትና ወደፊት መሻሻሎችን ማድረግ እንደሚገባው ተናግረዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ከሚገኘው ጉማራ የተሰኘ ወረዳ በምክክር ኮሚሽኑ የተሳተፉ አካል ጉዳተኛና አርሶአደር እንዲሁም አናሳ ማህበረሰቦች ናቸው ከተባሉት ውስጥ የተመደቡት አቶ አህመድ ሞሳ በበኩላቸው፤ በምክክር ኮሚሽኑ አካል ጉዳተኞች በመጠኑም ቢሆን መሳተፋቸውን አመስግነው፤የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ መብቶቻችን በውይይት የማስከበርን ዲሞክራሲያዊ ባህል ለማዳበር እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።
በተለይ በማህበረሰቡ በተሳሳተ አመለካከት ሰርጾ የቀረውን የመገለልና የማግለል ባህል በዘላቂነት ለማስወገድ የምክክር ኮሚሽኑ መጀመሩ መልካም አጋጣሚ መሆኑም ጠቁመዋል።
ቢሆንም ግን የምክክር ኮሚሽኑ የተካሄደው በሆሳዕና ከተማ በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በመሆኑ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አልነበረም ነው ያሉት።
በኦሮሚያ ክልል የሻሸመኔ እና አካባቢው ነዋሪ የሆነውና አካል ጉዳተኛው እሸቱ ተፈራ በምክክር ኮሚሽኑ ተሳትፏቸው ወቅት የታዘቡትን ሲገልጹ፤ የምክክር ኮሚሽኑ አካታችነትን በማሰብ እንዲሳተፉ ማድረጉን በበጎ ጎን እንደሚመለከቱት ገልጸው፤ ኮሚሽኑ አጀንዳ ለመስብሰብና ለማወያየት የሚጠቀማቸው ቦታዎች በአብዛኛው ለአካል ጉዳተኞች የማይመቹ ናቸው ብለዋል።
እንደምሳሌ ሲገልጹ፤ምክክር ኮሚሽኑ በአዳማ ከተማ ለውይይት የመረጠው ቦታ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየምንና አባገዳ የተሰኜ አዳራሽን ቢሆንም ሁለቱም በኮፕልስቶን ንጣፍና በመወጣጫ ደረጃዎች የተሞሉ እንጂ አካል ጉዳተኛን በምንም ሁኔታ ከቦታ ቦታ የማያንቀሳቅሱ ናቸው ብለዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በቦንጋ ከተማ ቦንጋ ዩንቨርስቲ አዳራሽ በሚገኝ ቦታ በምክክሩ የተሳተፉና ያነጋገርናቸው አቶ ሙራት ጀማል፤የሀሳብ ልዩነቶች የሰላም እጦትን፣ ግጭትን እና መፈናቀልን ሲያስከትሉ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚጎዱ ገልጸው፤በተለይም የዚህ ጉዳት ዋነኛ ሰለባዎች የአካል ጉዳተኞች በመሆናቸው በምክክር ሂደቱ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ችግሩን ለመፍታት ጥረት መኖሩ መልካም ነው ብለዋል።
አቶ ሙራት ጀማል መምህር መሆናቸውንና የመምህራኖችን ጥያቄ በውክልና ለምክክር ኮሚሽኑ ማቅረባቸውን ጠቁመው፤ መምህራን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከፋፈሉት የቀድሞው ደቡብ ክልል የነበሩት አካባቢዎች ላይ በርካታ ጥያቄዎች አሏቸው ብለዋል።
ከእነዚህም መካከል ደመወዝ በሚገባው ልክ እየተከፈለ አለመሆኑን ተከትሎ ለምክክር ኮሚሽኑ ጥያቄያችንን አቅርበናል ነው ያሉት።
ነገር ግን የትራንስፖርት ብር ማጣትን ጨምሮ ለአካል ጉዳተኞች የተለየ ሁኔታ ባለመመቻቸቱ ወደ ምክክር ኮሚሽኑ መምጣት ያልቻሉ በርካታ አካል ጉዳተኞች እና አናሳ የማህበረሰብ ክፍሎች ሳይሳተፉ መቅረታቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማሕበር አባል የሆኑት አቶ ተስፋው አወቀ በበኩላቸው ሃገራዊ ምክክሩ አካል ጉዳተኞችን አሳታፊ ማድረጉ የተሻለ ውጤታማ እንዲሆን እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
ምክክር ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ሲያደርገው ከነበረው አካታችነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደረገ ያለው የውይይት መድረክ በአካታችነት ዘርፉ የተሻለ ቢሆንም አሁንም በርካታ መሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ይናገራሉ።
አካል ጉዳተኞች እና በማህበረሰቡ በኩል የተገለሉ የማህብረሰብ ክፍሎች ተካታች ሁነዋል ከሚለው በስተጀርባ ለእነሱ የሚያመች ሁኔታን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።
በኢትዮጵያ በሀገር በቀል እውቀቶች ላይ የሚመራመሩና በማሕበረሰቡ በኩል በተገለሉ ሰዎች ላይ ትኩረታቸውን አድረገው የሚሰሩት ዶክተር አሉላ ፓንክረስት እንደገለጹት፤ በምክክር ኮሚሽኑ ከአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ በተጨማሪ በእደ ጥበብ የሚተዳደሩ እና በማህበረሰቡ በኩል የተገለሉ አነስተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ተጠቁሟል፡፡
እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች በሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማሳተፍ እንደሚገባቸው ዶክተር አሉላ ፓንክረስት ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ አነስተኛ የማህበረሰብ ክፍሎች በመኖራቸው የምክክር ኮሚሽኑ ደግሞ በደል እና ብሶት የሚቀርብበት እና ችግሮችን ተወያይቶ መፍትሔ እንዲመጣ የሚሰራ በመሆኑ እነዚህ ማህበረሰቦች ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባቸው አጽንዖኦት ሰጥተውበታል።
የምልክት ቋንቋ ለማስተርጎም በምክክር ኮሚሽኑ ያነጋገርናት አስተርጓሚዋ ማዕዶት ጥላሁን እንደምትገለጸው፤ የምክክር ኮሚሽኑ አካል ጉዳተኞችን አካታች በማድረግ እያሳተፈ መሆኑን ገልጻ፤ለአካል ጉዳተኞች ትልቅ እንቅፋት የሆነው የማህበረሰቡ አስተሳሰብ ነው ስትል ትናገራለች።
ነገ በሰው ሰራሽ ምክንያት ማንኛውም ሰው አካል ጉዳተኛ ሊሆን እንደሚችል እየዘነጉ ያሉት አንዳንድ አካላት፤ አካል ጉዳተኞች ምንም አይነት ተጽዕኖ እንደማይፈጥሩ እና በምክክር ኮሚሽኑ ቢሳተፉም ምንም ትርጉም እንደሌለው የሚያስቡ በርካታ ሰዎች አሉ ስትል ገልጻለች።
ይህን መሰል አስተሳሰብን መቅረፍ ከተቻለ ማንኛውም አካል ጉዳተኛ ለሃገሩ አስተዋጽዖ ማበርከት እንደሚገባው ግንዛቤ መወሰድ አለበት ስትል ትገልጻለች።
በኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማሪያም አካታችነትን በተመለከተ ከጣቢያችን ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ በሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን የአካል ጉዳተኞችን ለማሳተፍ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ቢሆንም ግን ዊልቸር ተጠቃሚ ለሆኑ አካል ጉዳተኞች የመሰብሰቢያ አዳራሾች አመችነት አለመኖሩ፤ በብሬል እና በድምጽ እንዲሁም በምልክት የተዘጋጄ መረጃ እጥረት መኖሩ ተግዳሮት እንደሆናቸው ኮሚሽነሩ ይገልጻሉ፡፡
በአብዛኛው ማህበረሰብ ክፍሎች በኩል ያለው አስተሳሰብ አካል ጉዳተኞች የሚያሳዝኑ እና እገዛ የሚፈልጉ እንጂ በምክክር ኮሚሽኑ ተሳታፊ እንደማይሆኑና ሃሳብ የማፍለቅ አቅም እንደሌላቸው ስለሚታሰብ በአብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ያን ያክል ትኩረት ሲሰጣቸው አለመስተዋሉ እንደተግዳሮት እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡
ቢሆንም ግን የምክክር ኮሚሽኑ ይሄን ሁሉ ተግዳሮት ተቋቁሞ አካል ጉዳተኞችን ተሳታፊ እያደረገ መሆኑንና በብሬል እና በድምጽ የታገዘ መረጃ ለማዘጋጀት እየተሞከረ መሆኑን ኮሚሽነር መላኩ ወልደ ማሪያም ገልጸዋል።
//ድምጽ-መላኩ ወልደ ማሪያም//
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከግንቦት ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ በክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት በ10 ክልሎች እና ከ2 በላይ በሆነ የከተማ አስተዳደሮች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ አጀንዳን በህዝባዊ ውይይቶች መሰብሰቡ ተመላክቷል።
ከዚህም ውስጥ የአካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ላይ መሳተፋቸው የተገለጸ ሲሆን አካል ጉዳተኞች እንዲሳተፊ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያትም፤በኢትዮጵያ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የአካል ጉዳተኞች እንደሚገኙና እነሱም በሀገሪቱ የስነ-ህዝብ ምጣኔ ከአንድ አስረኛ በላይ እንደሚሆኑ ጥናቶች እንደሚጠቁሙ አስታውሰው፤
እነዚህ በሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ በንቃት መሳተፋቸው ለእነሱ ምቹ የሆነች ሀገርን በመገንባቱ ረገድ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ዕድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።
ይህንን መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ቁልፍ ተዋንያን እንዲሆኑ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
በዚህ ረገድ ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቶቹ ላይ የሚሳተፉ የአካል ጉዳተኞችን ቢያንስ በ10 በመቶ ተወክለው የወከላቸውን የሕብረተሰብ ክፍል ሀሳብ በአደራ ይዘው ለኮሚሽኑ እንዲቀርቡ ኮሚሽኑ የአሰራር ስርዓቶችን መዘርጋቱንም አስታውቋል።
የአካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ በንቃት መሳተፋቸው ምን ጥቅም አለው ተብሎ ለምክክር ኮሚሽኑ ለቀረበለት ጥያቄ፤በሂደቱ ላይ ሊኖራቸው የሚገባውን የውክልና ኮታ በመጠቀም ድምፃቸውን ለማሰማት ምቹ አጋጣሚን እንደሚፈጥርላቸውና የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ሀሳቦችን በማቅረብ ለፖሊሲ ማሻሻያነት በግብዓትነት ሊቀርቡ እንደሚያስችልና በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ውስጥ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ መብቶቻቸውን በውይይት የማስከበርን ዲሞክራሲያዊ ባህል እንደሚያጎለብተው ጠቁመዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን ባካሄዳቸው የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ በሃገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በህግ ጥላ ስር የሆኑ ታራሚዎችን እስካሁን እየተሳተፉ አለመሆኑን ገልጿል።
ኮሚሽኑ ከዚህ በኋላ በቀሩት ክልሎች በሚያደርጋቸው የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራም በተገለሉ ማህበረሰቦችና አካል ጉዳተኞች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚሰራ ቃል ገብቷል።
ምላሽ ይስጡ