ታኅሳስ 08 ቀን 2017 ዓ.ም(መናኸሪያ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባው የውጭ ባንኮች በሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ የሚፈቅድ የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡
የፕላን፤ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኛ ወዳጄ ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
ሰብሳቢው የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ የውጭ ባንኮችን በሀገር ውስጥ በማሳተፍ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት በማድረግ የባንኮችን ተወዳዳሪነት እና ውጤታማነት በማሻሻል ለኢኮኖሚው ዕድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ በቂ የሆነ ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ፈቃድ መስጠቱ የሀገር ውስጥ ባንኮች ላይ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል መረዳት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ተቋማት ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው ጠቀሜታው እንዳለ ሆኖ በተለይ የግል ባንኮች ላይ ያለውን ተወዳዳሪነት እና አቅምን ያማከለ ረቂቅ አዋጅ መሆን እንዳለበት የምክር ቤቱ አባላት ጠቁመዋል፡፡
ብሔራዊ ባንክ የውጭ ባንኮችን ለመቆጣጠር እና ለማስተዳደር የሚያስችል ዘመኑን የዋጀ የዓሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚጠበቅበትም የምክር ቤት አባላት አሳስበዋል፡፡
የውጭ ባንኮች በሀገር ውስጥ የሚያፈሩትን ገንዘብ ወደ ሌላ ሀገራት እንዳያሸሹ ብሔራዊ ባንክ መከታተል እና መቆጣጠር እንዳለበት የምክር ቤት አባላት አመላክተዋል፡፡
የውጭ ባንኮች ከዲጅታል አሰራር ጋር በተያያዘ የሀገርን ሉአላዊነትና ደህንነት በጠበቀ መልኩ የፋይናንስ ስርአቱ እንዲመራ ብሔራዊ ባንክ በትኩረት መስራት እንዳለበት የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው፤ የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ በፋይናንስ ዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳደሪ ለመሆንና ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ ማለት በጋር እና በሽርክና ጭምር ከሀገር ውስጥ ባንኮች ጋር በትብብር የሚሰሩ መሆኑን መረዳት እንደሚገባ አቶ ማሞ ምህረቱ አስረድተዋል፡፡
የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጁ ለሀገር ውስጥ ባንኮችም የዕውቀት ሽግግር የሚፈጥር መሆኑን የባንክ ገዡ ጠቁመው፤ የሀገር ውስጥ ባንኮችም አቅማቸውን በማጎልበት ተወዳደሪ ለመሆን ሰብሰብ ብለው የፋይናንስ አቅማቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ባንኮችን ከመቆጣጠር እና ከማስተዳደር አንጻር በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት ብሔራዊ ባንክ በአግባቡ የሚወጣ መሆኑንም አቶ ማሞ ምህረቱ ገልጸዋል፡፡
ዲጅታላይዝ የባንክ አሰራር ከማሳደግ አንጻር እምርታዊ ለውጥ የታየበት እና ማህበረሰቡ ከጥሬ ገንዘብ በበለጠ በኤሌክትሮኒክስ የግብይት ስርዓቱ የተሻለ ልውውጥ እያደረገ የመጣ መሆኑን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
ምክር ቤቱ የቀረበለትን የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጁ፤ አዋጅ ቁጥር 1360/2017 አድረጎ በሶስት ተቃውሞ፤ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን ከምክርቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
መናኸሪያ ሬዲዮ 99.1
ሃሳብ፣አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት የሚከተሉትን የስቱዲዮ ስልኮቻችን ይጠቀሙ
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
የቀጥታ ስርጭት 👉 📻 (https://worldradiomap.com/et/play/menaharia) radio 99.1 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
✅ https://t.me/menaharia_fm
ትክክለኛውን የመናኸሪያ ሬዲዮ የዩቱዩብ አድራሻ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
➲ Youtube (https://www.youtube.com/channel/UC8uROsU69D8Ob65XapeHvIw)
ምላሽ ይስጡ