በኢትዮጵያ የግብርና ምርት ብክነትና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተግዳሮቶች
ግብርና የበርካታ አገራትን ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ያሳደገ፣ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር በፍጥነት እንዲሸጋገሩ ያደረገ መሆኑ ይታወቃል። እንደ ቻይና፣ አሜሪካ እና ሩሲያ ያሉ አገራት በግብርናው ዘርፍ የሜካናይዜሽን አሰራርን በስፋት በመጠቀም ተለውጠውበታል ሲሉ የግብርና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያም ምንም እንኳን በተፈጥሮ ባደላት የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የአፈር ለምነት ልክ ባይሆንም፣ በአፍሪካ በግብርናው ዘርፍ ጥሩ ደረጃ ላይ ከሚመደቡት አገራት ውስጥ እንደምትገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ። ይሁን እንጂ፣ ግብርናው ዋነኛ የገቢ ምንጯ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ የተሻለ ሜካናይዜሽን ከሚጠቀሙ እንደ አልጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካና ግብጽ ካሉ አገራት ጋር ተርታ መግባት አልቻለችም። ይህም ያላትን ለግብርና አመቺ የሆነ መሬት በዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ እንዳይታረስ አድርጎታል።
በድህረ ምርት ወቅት የሚባክነው መጠን አሳሳቢ ነው
በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ በውል የሚታወቅ የተሟላ ጥናት ባይኖርም፣ በድህረ ምርት ወቅት የሚባክነው የምርት መጠን ከፍተኛ ነው። አንዳንድ ጥናቶች ከሚመረተው ምርት ውስጥ ከ30 እስከ 35 በመቶ እንደሚባክን ሲገልጹ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአትክልትና ፍራፍሬዎች (እንደ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ማንጎ እና የመሳሰሉት) ላይ ያለው ብክነት ከ50 እስከ 70 በመቶ እንደሚደርስ ይገለጻል።
በጉዳዩ ላይ ሐሳባቸውን የሰጡት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ጥላሁን ለማ፣ በድህረ ምርትና በሰብል አሰባሰብ ወቅት የሚባክነው ምርት ከ30 በመቶ በላይ መሆኑ ከፍተኛ የሀገር ኪሳራ እንደሚያስከትል ያብራራሉ። ለምርት ብክነት ዋነኛ ምክንያቶች መካከል ባህላዊ የምርት አሰባሰብ ሂደት መከተል እና የዘመናዊ መሳሪያዎች እጥረት መሆናቸውን ጠቅሰዋል። አጠቃላይ የሰብል ብክነትን ለመቀነስ በድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎች ላይ መስራት፣ የቴክኖሎጂ ተቋማትና የግብርና ሚኒስቴር ችግር ፈቺ ምርምሮችን ማካሄድ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥርዓት መፍጠር እንደሚገባ አመላክተዋል።
የዓለም አቀፉ የእርሻ ድርጅት (FAO) በድህረ ምርት ወቅት 30 በመቶ ያህል የሰብል ብክነት እንደሚታይ በተደጋጋሚ እንደሚገልጽ የሚያነሱት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ናቸው። ክልሉ በአሁኑ ሰዓት ምቹ ምኅዳሮችን በመፍጠር ላይ ትኩረት እያደረገ መሆኑን ገልጸው፣ አርሶ አደሮች የግብርና መሳሪያዎችን በ40 በመቶ ቁጠባ እና በ60 በመቶ ብድር እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
የብክነት መንስኤዎች እና መፍትሄዎች
በኢትዮጵያ የድህረ ምርት ብክነት ማህበር አባል የሆኑት ዶክተር አሻግሬ ዘውዱ፣ ብክነቱ ከጥራጥሬዎች ባሻገር በተለይ ቶሎ በሚበላሹ እንደ ቲማቲም ባሉ ምርቶች ላይ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል። ዶ/ር አሻግሬ፣ የመሬት አቀማመጥ ለሜካናይዜሽን የማይመች ቢሆንም አምራች ለሆኑ አካባቢዎች ስልታዊ የሆነ የዘመነ ቴክኖሎጂ መጠቀም እንደሚገባ መክረዋል። በስብስብ ወቅት ከሚባከነው የምርት መጠን ባልተናነሰ በማከማቻ ቦታዎች (ጎተራዎች) በተባይ ተበልቶ የሚባክነው ቀላል እንዳልሆነም አንስተዋል። የምርምርና የቴክኖሎጂ ተቋማት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ለግብርናው ዘርፍ ብቁ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማስገኘትና ቀላል የመሰብሰቢያ መሳሪያዎችን ማቅረብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ፣ የሀገሪቱ የድህረ ምርት እንክብካቤ እጅግ ደካማ መሆኑን ገልጸው፣ ከ30 እስከ 35 በመቶ የሚሆነው ምርት እንደሚባክን ይገምታሉ። በተለይ እንደ ቲማቲምና ሽንኩርት ባሉ ምርቶች ላይ ከመሠረተ ልማትና ከተጠቃሚ ቁጥር ማነስ ጋር ተያይዞ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ምርት እንደሚባክን ያብራራሉ። የቴክኖሎጂ አምራች ተቋማትና የግብርናው ዘርፍ በቅጡ አለመተሳሰራቸው ዋነኛ ችግር መሆኑን ጠቅሰው፣ የኋላ ቀር የአስተራረስና የአሰባሰብ ዘዴን ማስቀረት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የመንግስትና የቴክኒክ ተቋማት ርብርብ
የኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር፣ ተቋሙ በሰልጣኞችና በአሰልጣኞች አማካኝነት ሚኒ ትራክተሮች፣ ክሬሸርና መውቂያ ማሽኖችን የመሳሰሉ ከውጭ ቢገቡ ውድ የሆኑ የግብርና መሳሪያዎችን የማምረት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ ከ80 በላይ የሚሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን አመላክተዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራ ተጠባባቂ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽመልስ ፀጋዬ፣ የድህረ ምርትን ብቻ ሳይሆን የቅድመ ምርትንም ጭምር በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አስረድተዋል። በትራክተር ደረጃ ከ19 ሺህ በላይ፣ 2 ሺህ 700 ኮምባይነር እንዲሁም 574 ሺህ የመስኖ ቴክኖሎጂዎች መኖራቸውንና በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የግብርና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማሰራጨት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ማጠቃለያ
በዚህ ዳሰሳ ጥናት ባለሙያዎቹ ባሳፈሩት ሐሳብ መሠረት፣ በጥራጥሬ ምርቶች በድህረ ምርት ከ30 እስከ 35 በመቶ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ደግሞ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚደርስ የምርት ብክነት በየዓመቱ ይከሰታል። ይህንን ለመቀነስ የግብርናውና የቴክኖሎጂ ተቋማት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ተመላክቷል።
በዘላለም አባት