ነሐሴ 08 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ)በቀጣዮቹ 6 ወራት ውስጥ የዲጂታል ነዋሪነት መታወቂያ ሕትመትና ሥርጭትን ወደ 60 አዳዲስ ወረዳዎች ለማስፋፋት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ አስታውቋል።
ቀደም ሲል የነዋሪነት መታወቂያዎች በማዕከልና በክፍለ ከተማ ደረጃ ብቻ ታትመው ይሰራጩ እንደነበር የሚናገሩት የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ ሹመይ፣ አሠራሩ አገልግሎት ፈላጊዎችን ለተጨማሪ ቀጠሮና እንግልት ይዳርግ እንደነበር ገልጸዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ የወረፋ ጫና ባለባቸው 22 ወረዳዎች ላይ በተደረገ የሙከራ ትግበራ፣ 1 ሺህ 432 ነዋሪዎች ወዲያውኑ መታወቂያቸውን መውሰድ መቻላቸውን ገልጸዋል።
አሠራሩን በማጠናከር በበጀት ዓመቱ አገልግሎቱን በከተማዋ ባሉ 119 ወረዳዎች በሙሉ አቅም ለመጀመር መታቀዱን የጠቀሱት አቶ ጥጋቡ፤ በቀጣዮቹ 6 ወራት ሕትመቱንና ሥርጭቱን ወደ 60 አዳዲስ ወረዳዎች ለማስፋፋት ዝግጅት መጀመሩን ተናግረዋል።
በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሕግ እስከ 5 ሺህ ብር የሚደርስ ቅጣት የተቀመጠ ቢሆንም፣ እስካሁን ቅጣቱን የማስፈጸም ሥራ እንዳልተጀመረ የገለጹት የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ፤ ዋናው ዓላማ ሕብረተሰቡን መቅጣት ሳይሆን ወሳኝ ኩነቶችን በወቅቱ የማስመዝገብ ግዴታ እንዳለ በማስታወስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መስራት እና የምዝገባ ባህልን ማዳበር ነው ብለዋል።
ወሳኝ ኩነቶችን በተቀመጠላቸው የ90 ቀናት ጊዜ ገደብ ውስጥ ማስመዝገብ ለግለሰቦች መብት መከበርና ለመንግሥት ዕቅድ ወሳኝ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የምዝገባ ሽፋኑ እየጨመረ ሲሄድ ግን ሕግ የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም የወሳኝ ኩነት ምዝገባን በወቅቱ ያላስመዘገበ አካል ይቀጣል ቢልም፣ እስካሁን ቅጣቱን ተግባራዊ ማድረግ አለመጀመሩን ገልጿል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ