ጥቅምት 26 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በመዲናይቱ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስታንዳርዱን የጠበቀ የቆሻሻ መጣያ (ደስት ቢን) እንዲተከል ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑ ይገለፃል፡፡
የኮሪደር ልማቱ ባልተጀመረባቸው አካባቢዎችም የቆሻሻ ማስወገጃዎቹ እንዲተከሉ የአዲስ አበባ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
የቆሻሻ ማስወገጃዎቹ ከተማዋን ንፁህ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያላቸው ቢሆኑም እየተሰረቁ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙላት ተገኝ ገልጸዋል፡፡
የቆሻሻ መጣያዎቹ ከብረት የተሰሩ በመሆኑ በከፈተኛ ሁኔታ እየተሰረቁ እንዳለ የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ ለእይታ ማራኪ የሆኑ የተሻሻሉ ዲዛይኖችን ከመጠቀም ባለፈ ለስርቆት እንዳይጋለጡ ሊቀልጡ የማይችሉ ቁሶች ጥቅም ላይ እንዲወውሉ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ልማዱ እንዲሻሻል ከሚሰራው የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ባለፈ ኮሪደር ልማቱ ተደራሽ ባልሆነባቸው አከባቢዎች አዳዲስ የቆሻሻ መጣያዎች እንዲተከሉ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ኤጀንሲው ከፍተኛ የሰዎች እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው በመገናኛ፣ ላምበረት፤ ኮተቤ እንዲሁም ወሰን መስመሮች ላይ ወደ 3ሺህ የሚሆኑ የቆሻሻ መጣያዎች መተከላቸውን እና በቀጣይም ውስጥ ለውስጥ በሚገኙ የአስፓልት መንገዶች ዳር ለመትከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የማህበረሰቡን የቆሻሻ አወጋገድ ልማድ ለማሻሻል ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ ባለው መዋቅር ባለሙያዎች ተመድበው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ