ጥቅምት 22 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በታንዛኒያ ባለፉት ሦስት ቀናት ውስጥ በምርጫው ውጤትና ሂደት ላይ በተነሳው ተቃውሞ ምክንያት በተፈጠረ ግጭት ሳቢያ፣ ወደ 700 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸውን ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ አስታውቋል።
ይህ ከባድ የሰው ሕይወት መጥፋት የተመዘገበው የኢንተርኔት መቆራረጥ በታየበትና የውጭ ጋዜጠኞችን የመዘገብ ሥራ ገደብ ባጋጠመው ወቅት ውስጥ ነው።
ዋናው ተቃዋሚ ፓርቲ የሆኑት ቻዴማ (Chadema) ባወጡት መግለጫ መሠረት፣ በንግድ ማዕከሏ በዳር ኤስ ሰላም ብቻ ወደ 350 የሚጠጉ ሰዎች ሲሞቱ፣ በምዋንዛ (Mwanza) ደግሞ ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።
የፓርቲው ቃል አቀባይ ጆን ኪቶካ እንዳሉት፣ ግድያው በሌሊት የሰዓት እላፊ ገደብ ወቅት ሊጨምር ይችላል።
ይሁን እንጂ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሰብአዊ መብት ጽ/ቤት በበኩሉ “አስተማማኝ ዘገባዎች” የሚላቸውን በመጥቀስ፣ በዳር ኤስ ሰላም፣ በሽንያንጋ እና በሞሮጎሮ አካባቢዎች የፀጥታ ኃይሎች የጦር መሳሪያና አስለቃሽ ጭስ በመጠቀማቸው ቢያንስ 10 ሰዎች መገደላቸውን ጠቁሟል። ይህም በተቃዋሚዎችና በዓለም አቀፍ አካላት ሪፖርቶች መካከል የሟቾች ቁጥር ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው ያሳያል።
ይህ ሁከት የተከሰተው ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሃሰን የገዢውን ፓርቲ (CCM) በመወከል በተግባር ተወዳዳሪ ባልነበሩበት የምርጫ ሂደት ሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማስጠበቅ በሞከሩበት ወቅት ነው።
ዋናው ተቃዋሚ ፓርቲ የሆነው ቻዴማ፣ መሪው ቱንዱ ሊሱ በክህደት ወንጀል ተከስሰው መታሰራቸውን ተከትሎ፣ ከምርጫው ውድድር ውጭ እንዲሆን በመደረጉ ምህዳሩ ተገድቦ ነበር።
ተንታኞች እንደሚሉት፣ ፕሬዚዳንት ሃሰን ይህንኑ የምርጫ ሂደት በመጠቀም ሥልጣናቸውን ለማጠናከርና በፓርቲያቸው ውስጥ ያሉ ተቺዎችን ድምፅ ለማፈን ጥረት አድርገዋል።
ተቃዋሚዎች የምርጫውን ሂደት ፍትሐዊ አለመሆን በመቃወም ተቃውሞ ሲያሰሙ፣ በፀጥታ ኃይሎችና በዜጎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ለከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት ሆኗል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ