ጥቅምት 20 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ የሚያስከትለው የጤና ቀውስ እየተባባሰ በመምጣቱ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ላይ ቁጥጥር የሚያደርገው አዋጅ በጠንካራ ይዘት እንዲጸድቅ ጠንካራ ድጋፋቸውን አሳውቀዋል።
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚከሰቱ ሞት ውስጥ ከግማሽ በላይ (52%) የሚሆነውን ድርሻ ይይዛሉ። በየሰዓቱ፣ ወደ 25 የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን በስኳር በሽታ፣ በኩላሊት፣ በጉበት እና በልብና የደም ዝውውር በሽታዎች ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ።
የተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ኢኮኖሚያዊ ሸክም ከባድ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግስትን በየዓመቱ 31.3 ቢሊዮን ብር እንደሚያስወጣ ይገመታል።
ይህ አሳሳቢ ሁኔታ የሀገሪቱን የህዝብ ጤና እና የኢኮኖሚ የወደፊት ዕጣ አደጋ ላይ ከመጣሉ በፊት ‘የጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ቁጥጥር አዋጅ’ በአስቸኳይ መጽደቅ እንዳለበት የሲቪል ማህበራት ጥምረት ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ የምግብ አቅርቦት ሁኔታ በፍጥነት እየተለወጠ፣ በፋብሪካ የተዘጋጁ ምግቦች በስፋት እየተበራከቱ ነው። ዓለም አቀፍ የምግብ ኩባንያዎች ጤናማ ያልሆኑ ምርቶቻቸውን በተለይም ለህጻናት በኃይል እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
በዚህም ምክንያት፣ የሲቪል ማህበራት የመራቢያ ጤና ማህበራት ጥምረት (CORHA)፣ የኢትዮጵያ የልብ ማህበር፣ የኢትዮጵያ የስኳር በሽታ ማህበር እና የኢትዮጵያ የኩላሊት ማህበር የአዋጁ የመጨረሻ ረቂቅ የሚከተሉትን ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች እንዲያካትት አጥብቀው አሳስበዋል፡፡
ከእነዚህም መካከል ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ምክረ ሃሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ የኢንዱስትሪ ትራንስ-ፋቶችን ማስቀረት እንዲሁም ሸማቾች ስለ ምግቦች የንጥረ ነገር ይዘት (ስኳር፣ ጨው፣ ስብ) ግልጽና በቀላሉ ለመረዳት የሚያስችል መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡
ጤናማ ያልሆኑ ምግቦች ለህጻናት እንዳይተዋወቁ ሙሉ በሙሉ መከልከል እና ጠንካራ የቁጥጥር ስልቶችን መዘርጋት እንደሚያስፈልግ የተመላከተ ሲሆን፤ የመንግስት ተቋማት እና ትምህርት ቤቶች የጤና መስፈርቶችን የሚያሟሉ እና ከአገር ውስጥ የሚመነጩ የተመጣጠኑ ምግቦችን ብቻ እንዲያቀርቡ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
የተጠቀሱት ማህበራት አዋጁ እንዲጸድቅ በሚያቀርቡት ጥሪ፣ የፖሊሲ አውጪዎች፣ የህግ አውጭዎች፣ ሚዲያዎች እና የሲቪል ማህበረሰብ አባላት ሁሉ ለጋራ ጤንነት እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል። በመጪዎቹ ወራትም የህዝቡን ግንዛቤ ለመፍጠር ሰፊ የሚዲያ ዘመቻ እንደሚያካሂዱ አስታውቀዋል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ