ጥቅምት 11 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)በአማራ ክልል በየሳምንቱ ከ200 በላይ ሰዎች በእብድ ውሻ በሽታ እየተጠቁ መሆኑን የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለመናኸሪያ ሬድዮ አስታውቋል፡፡
በክልሉ በእብድ ውሻ በሽታ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሆነ በኢንስቲትዩቱ የአንድ ጤና ምልከታ ማስተባበሪያ የሙያተኞች ቡድን ሰብሳቢ አቶ ሀብታሙ አለባቸው ተናግረዋል፡፡
በ2017 በጀት አመት በክልሉ ከ80 በላይ ሰዎች በበሽታው ምክንያት ህወታቸው ማለፉን የሚናገሩት ሰብሳቢው፤ ከ7ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ለበሽው ተጋላጭ እንደነበሩ ገልፀዋል፡፡
የ2018 በጀት አመት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በየሳምንቱ ከ200 በላይ ሰዎች በእብድ ውሻ በሽታ እየተያዙ እንደሆነና በአማካኝ 3 ሰዎች ህይወታቸው እንዳለፈ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ በእብድ ውሻ በሽታ ተይዘው ወደ ጤና ተቋማት የሚያመሩ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን የሚናገሩት አቶ ሀብታሙ፤ በክልሉ በቂ ህክምና እንደሌለና የጤና ባለሙያዎች የቅድመ ድህረ ተጋላጭነት ክትባት አለመከተባቸው እንዲሁም ለታካሚዎች የአስተኝቶ ህክምና መስጫ አለመኖሩ አሁንም ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል ብለዋል፡፡
በመሆኑም በክልሉ የእብድ ውሻ በሽታን ተከትሎ የተኝቶ ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ባለመሆኑ ታማሚዎች በቤታቸው ውስጥ ህይወታቸው እያለፈ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ህብረተሰቡ የሚያሳድጋቸውን ውሾች አለማስከተቡ ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት መሆኑን የሚናገሩት ሰብሳቢው፤ በተለይ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል የእብድ ውሻ በሽታ እየተስፋፋ በመሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች ራሳቸውን ከበሽታው ስርጭት እንዲጠብቁ አቶ ሃብታሙ ጠይቀዋል፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ