ጥቅምት 11 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የአርሰናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ተከላካዩ ፒዬሮ ሂንካፒዬ ለዛሬው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተጠባቂ ጨዋታ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የክለቦች ትልቁ የውድድር መድረክ የሆነው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሶስተኛ ዙር ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ የሚካሄዱ ይሆናል። ከተጠባቂዎቹ ጨዋታዎች መካከል መድፈኞቹ አርሰናል በሜዳቸው ኤምሬትስ ስቴዲየም ከዲዬጎ ሲሚዮኒ ጠንካራ ቡድን አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
እስካሁን የተደረጉትን ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ ስድስት ነጥብ ከሰበሰቡት ስድስት ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው አርሰናል፣ ሶስተኛ ጨዋታውንም ለማሸነፍ ጥረት የሚያደርግበት ነው። ሮጂብላንኮዎቹ በበኩላቸው አንድ ጨዋታ ተሸንፈው አንድ ጨዋታ በማሸነፍ በምድባቸው 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ይህንን ጨዋታ ያከናውናሉ።
ሁለቱ ክለቦች ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በአርሰን ቬንገር የመጨረሻ የአሰልጣኝነት ዘመን፣ በዩሮፓ ሊግ የደርሶ መልስ ጨዋታ ነበር። ያኔ አትሌቲኮ ማድሪድ በድምር ውጤት 2-1 በማሸነፍ ወደ ፍፃሜው ካለፈ በኋላ ዋንጫውንም ማሳካት መቻሉ ይታወሳል።
የአርሰናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በየትኛውም የጨዋታ መድረክ ከዲዬጎ ሲሚዮኒ ጋር ተገናኝቶ አያውቅም፤ ስለዚህ የዛሬው ፍልሚያ የመጀመሪያ ግንኙነታቸው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ኤኳዶሪያዊው አዲሱ ግዢያቸው ፒዬሮ ሂንካፒዬ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ እንደሚሆን አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ አረጋግጠዋል። ተጫዋቹ ባለፈው ወር የሊግ ካፕ ጨዋታ ሲያከናውን በብሽሽት ጉዳት ምክንያት ከሜዳ ውጪ ሆኖ ነበር። ከእርሱ በተጨማሪ ካይ ሃቨርትዝ፣ ኖኒ ማዱዌኬ እና ገብርኤል ጄሱስ ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል መቃረባቸውንና የአካል ብቃት እንቅስቃሴያቸውን (Fitness) እየሰሩ መሆኑንም አርቴታ ተናግረዋል።
አትሌቲኮ ማድሪድ በጣም ጠንካራ ቡድን መሆኑን እና ጥሩ ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾች እንዳሉት የገለጹት የአርሰናሉ አሰልጣኝ፣ ይህ ጨዋታ የቡድናቸውን ወቅታዊ አቋም ለመገምገም ከፍተኛ ወሳኝነት እንዳለውም አክለዋል።
ሁለቱም ቡድኖች ያለፉትን አምስት ጨዋታዎች ሳይሸነፉ በመቆየታቸው ወቅታዊ አቋማቸው ጥሩ በመሆኑ፣ የዛሬው ጨዋታ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል። ጨዋታው ምሽት 4:00 ሰዓት ሲጀምር ጣሊያናዊው ዳኛ ዳቪዴ ማሳ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አትሌቲኮ ማድሪድ በኤምሬትስ ስታዲየም ሙቅ ሻወር መከልከሉን ተከትሎ ለአውሮፓ እግርኳስ ማህበር (UEFA) ቅሬታ ማቅረቡ ተዘግቧል። ከዛሬው ጨዋታ በፊት ትላንት ምሽት በኤምሬትስ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዳቸውን ካከናወኑ በኋላ፣ ሰውነታቸውን ለመታጠብ ወደ ሻወር ቤት ሲሄዱ ሙቅ ሻወር ማግኘት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት ተጫዋቾቹ ከነላባቸው ወደ ሆቴላቸው ለመመለስ ተገደዋል። አንድ አስተናጋጅ ክለብ ሊያሟላቸው የሚገቡ አገልግሎቶችን አርሰናል ባለማሟላቱ ቅሬታቸውን ለዩሮፓ እግር ኳስ ማህበር (UEFA) አቅርበዋል። ጉዳዩ ሆን ተብሎ ተጫዋቾቹ ምቾት እንዳይሰማቸው የተደረገ ከሆነ፣ አርሰናል ለቅጣት ሊዳረግ እንደሚችልም ተገልጿል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ