ጥቅምት 04 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)በማዳጋስካር እየተባባሰ የመጣውን የፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ፣ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ከስልጣናቸው በመልቀቅ ከሀገር መውጣታቸው ተዘገበ። ፕሬዚዳንቱን ለቀው እንዲሸሹ ያስገደዳቸው ዋነኛ ምክንያት፣ ተቃውሞውን ለመግታት ተሰማርቶ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት ክፍል ወደ ሕዝባዊው የፀረ-መንግሥት ተቃውሞ ጎራ መቀላቀሉ ነው ተብሏል።
ለሳምንታት በዋና ከተማይቱ አንታናናሪቮ ሲካሄድ የነበረው ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ከትናንት በስቲያ በሀገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ውስጥ ከፍተኛ መከፋፈልን አሳይቷል። በመንግሥት ላይ ቅሬታ የነበራቸው ቁልፍ የጦር አዛዦች የሚመሩት ወታደራዊ ክፍል፣ በግልጽ ለተቃዋሚዎች ድጋፍ መስጠቱን ካወጀ በኋላ፣ ሁኔታው የመንግሥትን የቁጥጥር አቅም ሙሉ በሙሉ አሳጥቷል።
ፕሬዚዳንቱ ሁኔታዎች መባባሳቸውን ተከትሎ የደህንነታቸውን ጉዳይ ከግምት ውስጥ በማስገባት ትናንት ምሽት አውሮፕላን ተሳፍረው ከሀገር መውጣታቸውን የመንግሥት ምንጮች በይፋ አረጋግጠዋል። ሆኖም የተጠለሉበት ሀገር እስካሁን በይፋ አልተገለጸም።
በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ምህዳር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የዋለ ሲሆን፣ የተቃዋሚ ኃይሎች አሁን ባለው ሁኔታ ጊዜያዊ አስተዳደር ለመመስረት እየተመካከሩ መሆናቸው ተሰምቷል። የዓለም ዓቀፍ ማኅበረሰብ ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን እና ወደ ሰላማዊ ሽግግር እንዲመጣ ጥሪ ማቅረቡም ተነግሯል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ