መስከረም 21 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ በመጪው እሁድ ለሚከበረው የሆራ አርሰዲ በዓል ወደ ከተማዋ የሚያቀኑ 10 ሚሊየን የሚጠጉ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት መደረጉን የከተማው ቱሪዝም ኮሚሽን ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል።
የቢሾፍቱ ከተማ የቱሪዝም ኮሚሽን ሀላፊ አቶ ደጄኔ በድሮ፤ በከተማው በአሉን ለማክበር 10 ሚሊየን የሚጠጉ ታዳሚዎች ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠብቅና እንግዶቹ የተሟላ አገልግሎት አግኝተው እንዲመለሱ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በአሉን በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በከተማው በኩል ሰፋፊ ስራዎች እንደተሰሩ እና ከበአሉ አስቀድሞ ማህበረሰቡ እንግዳ እንዲቀበል ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
በዓሉ ከተማዋ ያሏት የቱሪስት መስቦች እንዲተዋወቁ እድል የሚፈጥር መሆኑን የገለጹት ሀላፊው፤ ከሰላም ማስከበር እና የተጋነነ የአገልግሎት ክፍያን ከመቆጣጠር አንጻር ህገ-ወጥ ተግባር እንዳይኖር ቁጥጥር እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
ለኢሬቻ ክብረ በዓል 10 ሚሊየን የሚገመቱ ዜጎች ወደ ከተማዋ የሚያቀኑ በመሆኑ ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃት እንደሚኖር የገለጹት ሀላፊው፤ በመሆኑም መደበኛ አገልግሎት ከሚሰጡ ሆቴሎችና ሌሎች ድርጅቶች ባሻገር ወጣቱ ተደራጅቶ እንግዶችን በማስተናገድ ገቢ የሚያገኝበት ሁኔታ መመቻቸቱንም አክለዋል።
የኢሬቻ ክብረ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉን የገለጹት ኃላፊው፤ ማንኛውም ስጋት ካለ በነጻ የስልክ መስመር 9671 ላይ በመደወል ጥቆማ ማቅረብ እንደሚቻል አስታውቀዋል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ