መስከረም 07 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ) የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች አዲስ ማሳሰቢያ ይፋ አድርጓል፤ ይህም በቱሪስት ቪዛ (B-1/B-2) ወደ አሜሪካ በመጓዝ በዚያ ልጅ የመውለድ ልምድ ላይ ያተኮረ ነው። ኤምባሲው እንዳስታወቀው፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይህን የቱሪስት ቪዛ ተጠቅመው ወደ አሜሪካ በመሄድ ልጅ ይወልዳሉ፤ ከዚያም ለህክምና ወጪያቸውም የመንግስት የገንዘብ ድጋፍ (ሜዲኬይድ) ይጠቀማሉ ብሏል።
ይህ ልምድ በዋናነት የአሜሪካን ግብር ከፋዮችን ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ እንደሆነ ኤምባሲው አብራርቷል። በተጨማሪም፣ በዚህ መንገድ የገቡ ግለሰቦች ለወደፊት የአሜሪካ ቪዛ ለማደስ ሲያመለከቱ የቪዛ አሰራራቸው ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል ተጠቁሟል።
ኤምባሲው አጽንኦት የሰጠው ፣ የቱሪስት ቪዛ ዋና ዓላማ ቱሪዝም፣ የንግድ ጉዳዮች፣ የህክምና ቀጠሮ (በግል የገንዘብ አቅም) እና የቤተሰብ ጉብኝትን የሚደግፍ እንጂ ልጅ የመውለጃ አገልግሎትን ለማግኘት አለመሆኑን ነው። የቱሪስት ቪዛን ለህጻናት መውለጃ አገልግሎት የመጠቀም ልምድ፣ ከቪዛ ህጎች ጋር የማይጣጣም ከመሆኑም በላይ፣ ለወደፊት የጉዞ ዕቅዶች ችግር ሊፈጥር እንደሚችልም ኤምባሲው አሳስቧል።
ስለሆነም፣ አሜሪካን ለመጎብኘት ያሰቡ ኢትዮጵያውያን የቪዛውን ትክክለኛ ዓላማ እንዲያከብሩ እና ለጉዞአቸውም ተገቢውን የቪዛ አይነት እንዲጠይቁ ኤምባሲው አሳስቧል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ