መስከረም 07 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ)ከዘመናዊው ዓለም ግርግርና ውጥረት ርቀው የአእምሮ እረፍት የሚሹ ሰዎች መዳረሻ የሆነ አዲስ የካፌ ጽንሰ ሃሳብ በጃፓን እየተስፋፋ ነው። እነዚህ ‘ጸጥታ ካፌዎች’ (Silent Cafés) በመባል የሚታወቁት ልዩ ቦታዎች፣ ደንበኞች እንዳይነጋገሩ በመከልከል ፍጹም የሆነ ጸጥታና መረጋጋት ይሰጣሉ።
የእነዚህ ካፌዎች ዓላማ ሰዎች ለራሳቸው ብቻ ጊዜ እንዲሰጡ፣ መጽሐፍ እንዲያነቡ ወይም በቀላሉ አእምሯቸውን እንዲያሳርፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው ተብሏል። በካፌዎቹ ውስጥ ትዕዛዝ መስጠት የሚቻለው በጽሑፍ በተዘጋጁ ወረቀቶች ላይ በመሙላት ወይም በምልክት ቋንቋ ብቻ ነው። ይህ አሰራር ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት በመቀነስ፣ አንድ ሰው ከራሱ ጋር ብቻ እንዲሆን ዕድል ይሰጣል ተብሏል።
የኦሳካው ሾጆ ካፌ እና የቶኪዮው ካፌ ዊዛውት ዎርድስ (A Cafe Without Words) የዚህ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ምሳሌዎች ናቸው። እነዚህ ቦታዎች በጠረጴዛዎች መካከል በቂ ርቀት በመጠበቅ፣ ምቹ ወንበሮችን በማቅረብ እና ከበስተጀርባ የሚሰሙ የሙዚቃ ድምጾችን እንኳን ሙሉ በሙሉ በማስወገድ የተረጋጋ ሁኔታን ይፈጥራሉ።
አንዳንድ የካፌዎቹ ደንበኞች እንደሚሉት፣ ይህ አካባቢ ለፈጠራ ሥራቸው መነሳሳት የሚሰጥ ወይም ከዕለታዊ ጫና ለመላቀቅ የሚያስችል ልዩ ልምድ ይሰጣቸዋል ተብሏል። ይህ የካፌ አይነት በግለሰባዊ ልምድ እና ውስጣዊ ሰላም ላይ ያተኮረ በመሆኑ፣ በሥራ ብዛት ለተጨናነቀው የጃፓን ማኅበረሰብ አዲስ አማራጭ ሆኗል ነው የተባለው።
ይህ አዲስ የንግድ ስራ ሞዴል በሌሎች አገሮችም ትኩረት እያገኘ ሲሆን፣ ከዘመናዊው የአኗኗር ዘይቤ ጋር የተያያዘውን የአእምሮ ጤና ፈተና ለመቋቋም የሚረዳ መፍትሄ ሆኖ ይታያል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ