ነሐሴ 19 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የኑሮ መጋራት በሚል በተለያዩ ዘርፎች ላይ በቀጥታ 14.5 ቢሊዮን ብር ድጎማ መዘጋጀቱን የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ገልጿል።
ይህ የተደረገው በተለይም ለመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ከተደረገ በኋላ ሊኖር የሚችለውን የዋጋ ንረት ለመከላከል በማሰብ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታውቋል።
ከመደበኛ ትምህርት ምገባ ጋር በተገናኘ 800,000 ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የታቀደ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ለደንብ ልብስም 1 ሚሊዮን ተማሪዎች ድጎማ ለማድረግ 5.6 ቢሊየን ብር እንደተመደበ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለመንግስት ሰራተኞች የሚሆን የቤት ኪራይ እና በመስሪያ ቤታቸው ላይ የምግብ ቤት ድጎማ እንደሚደረግ የተገለጸ ሲሆን፣ ለፐብሊክ ባስ እና ለቀላል ባቡርም ድጎማ እንደሚደረግ ኃላፊው ተናግረዋል።
ከማህበራዊ አገልግሎቶች ጋር በተገናኘ ለጤና መድን እና ለሸገር ዳቦም ድጎማ እንደሚደረግ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም የመዲናዋ ነዋሪዎች የኑሮ ውድነት እንዳይገጥማቸው ታስቦ እንደሆነ ተመላክቷል።
በኢቫን ስለሺ
ምላሽ ይስጡ