ነሐሴ 19 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ቀጥተኛ ድርድር ማድረግ የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ እጅግ ውጤታማው መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ጦርነቱን ለማቆም የሚደረገው ጥረት ቢዘገይም ከፑቲን ጋር መነጋገር “ወደፊት ለመራመድ እጅግ ውጤታማው መንገድ” ነው ብለዋል። ምንም እንኳ ሞስኮ በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ስብሰባ እንደማይኖር ብትገልጽም፣ ዘለንስኪ በዩክሬን የነጻነት ቀን ንግግራቸው ላይ ይህን አቋማቸውን በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ይህ የዘለንስኪ ጥሪ በአሜሪካ እና በሌሎች ምዕራባውያን አጋሮች አማካኝነት ለሰላም ድርድር ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት የመጣ ነው። ይሁን እንጂ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ የምዕራባውያንን የድርድር ጥረት እያደናቀፉ ነው በማለት ወቅሰዋል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የዩክሬንን ነጻነት ማረጋገጥ እና ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ጥቃቶችን ለመከላከል ምዕራባውያን አገሮች ለዩክሬን የደህንነት ዋስትና እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል። ይህም የአገሪቱን ሉዓላዊነት እና ነጻነት ለመጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።
የሁለቱ አገሮች ወታደራዊ ግጭት ቀጥሎ ባለበት ሁኔታ፣ ዩክሬን እና ሩሲያ በቅርቡ እያንዳንዳቸው 146 የጦር እስረኞችን እና ሲቪሎችን መለዋወጣቸው ተገልጿል። ይህ የጦር እስረኞች ልውውጥ በሁለቱ አገሮች መካከል የቀረ ብቸኛ የትብብር መስመር መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ።
በጌታሁን አስናቀ
ምላሽ ይስጡ