ነሐሴ 13 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ከመሰከረም ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ እንደሚያደረግ መንግስት የወሰነው ውሳኔ የሚበረታታ ቢሆንም ከደመወዝ ጭማሪው ባለፈ የዋጋ ንረት ላይ እና ዜጎች ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበትን አማራጮች የማስፋት ስራዎችን መስራት እንደሚገባ መናኸሪያ ሬዲዮ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ጉቱ ቴሶ መንግስት ባለፉት አስርት አመታት ከታየው የዋጋ ንረት አንፃር ቀደም ሲል መንግስት ያደረገው ጭማሪ በቂ እንዳልሆነ በመገንዘብ ማስተካከያ ማድረጉ የሚበረታታ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ምንም እንኳ ባለፉት ጊዜያት መንግስት የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር እየሰራ መሆኑንና መረጋጋቶች መኖራቸውን እየገለጸ ቢሆንም ፤ ሀገሪቷ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የዋጋ ንረት ያለባት ሃገር እንደሆነች መረጃዎች ያመላክታሉ።
ከዚህ መነሻነት ከደመወዝ ጭማሪው ባሻገር የዋጋ ንረቱን መቆጣጠርና ዜጎች ተጨማሪ ገቢ የሚገኙባቸውን አማራጮች ማስፋት አጠቃላይ የሀገሪቷን ዜጎች ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እንደሚያደረገው አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የሰላሙን ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ቴክኖሎጂዎችን ማስፋትና ለስራ ፈጣራ ያለንን ግንዛቤ ማስተካከል እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
ሌለኛው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዶክተር አጥላው አለሙ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ከተደረገው ጭማሪ ያሁኑ የተሻለ ነው ካሉ በኋላ ይህ ማለት ግን የሠራተኛውን ጥያቄ ምላሽ አገኘ፤የመጨረሻው ነው ማለት እንደማይቻልና ዘላቂ መፍትሄው የዋጋ ግሽበትን የሚያመጡ ነገሮችን መቆጣጠር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የወጪ ቁጠባ ስራዎች በመንግስት በኩል መኖር እንዳለባቸውና ከዚህ ቀደም ያለአግባብ ታትመው ገቢያው ላይ የተበተኑ ገንዘቦች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
አሁን የተደረገው የደመወዝ ማስተካከያ ከ160 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት እንደሚጠይቅና መንግስት ለደመወዝ የሚወጣውን ጠቅላላ ዓመታዊ ወጪ 56ዐ ቢሊዮን እንደሚያደረሰው ተመላክቷል፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ