ነሐሴ 08 ቀን 2017 (መናኸሪያ ሬዲዮ) የቻይና ጦር በደቡብ ቻይና ባህር አወዛጋቢ በሆነው የሀዋንያን ደሴት አቅራቢያ በቻይና የባህር ክልል ውስጥ ያለ ፈቃድ ገብቶ ነበር ያለው የአሜሪካ የጦር መርከብ (USS Higgins) መባረሩን አስታውቋል።
የህዝብ ነጻነት ጦር (PLA) የደቡብ ቲያትር ኮማንድ ቃል አቀባይ ከፍተኛ ካፒቴን ሄ ቲየንቸንግ፣ የዩኤስ የጦር መርከብ የቻይናን ሉዓላዊነትና ደህንነት በእጅጉ እንደጣሰ ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ የቻይና የባህር ኃይል እና አየር ኃይል መርከቡን ለመከታተል፣ ለማስጠንቀቅና ለማስወጣት በህግና ደንብ መሰረት እርምጃ ወስደዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ሰባተኛው ፍሊት በበኩሉ፣ ቻይና የሰጠችው መግለጫ “ሀሰት” ነው ብሎ ውድቅ አድርጎታል። የአሜሪካ የባህር ኃይል እንደገለጸው፣ መርከቡ “በአለም አቀፍ ህግ መሰረት የአሰሳ መብቱንና ነጻነቱን” እያረጋገጠ ነበር ብሏል።
በደቡብ ቻይና ባህር ላይ በቻይናና በሌሎች ሀገራት መካከል ያለው ግጭት ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ሲሆን፣ በተደጋጋሚም በሁለቱ ሀያላን ሀገራት መካከል ከፍተኛ ውጥረት ይፈጠራል ተብሏል።
ይህ የቅርብ ጊዜ ክስተት የተከሰተው ደግሞ የቻይና የባህር ጠባቂ መርከቦች ከፊሊፒንስ መርከቦች ጋር ግጭት ውስጥ ከገቡ በኋላ ሲሆን፣ ይህም በክልሉ ያለውን አለመረጋጋት የበለጠ አባብሶታል ተብሏል።
ምላሽ ይስጡ