ነሐሴ 01 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ ባለፉት ሁለት የክረምት ወራት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደነበራቸው የኢትዮጵያ ሜትሮዎሎጂ ኢኒስቲትዩት አስታውቋል።
የወቅቱ የዝናብ አጀማመርም ትንበያ በተሰጠው መሠረት በተለይም ደቡብ ምዕራብ፤ ምዕራብና መካከለኛው አከባቢዎች ላይ ቀድሞ እንደጀመረና ይህ ሊሆን የቻለበት ዋናኛው ምክንያት በትሮፒካል ፓስፊክ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ የባህር ወለል ሙቀት እንዲሁም የሰሜናዊ ህንድ ውቅያኖስ መደበኛ የባህር ወለል ሙቀት መጠን በመሆኑ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደነበረው ተጠቅሷል፡፡
በተለይም ባለፉት ሁለት ወራት በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ የተስተዋለ ሲሆን በአጠቃላይ ሁለት መቶ ሀያ ሰባት በሚደርሱ የሀገራችን አከባቢዎች ላይ በ24 ሠዓት ውስጥ ከ30 እስከ 127 ሚሊ ሜትር ዝናብ ተመዝግቧል፡፡
በአጠቃላይ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች የትግራይ፣አማራ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ፣ሀረርና ድሬደዋ ሰሜን ሶማሌ ላይ ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደነበራቸው ተገልጿል።
ይህ ሁኔታ በክረምት ወቅት ለሚከናወኑ የግብርና ስራን ለማከናወን እንዲሁም የተለያዩ ተፋሰሶች የውሃ መጠን እንዲሻሻልና ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደነበረው ተጠቅሷል ።
በቀሪዎቹ የክረምት ወራትም የትሮፒካል ፓስፊክ ውቅያኖስ ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ የባህር ወለል ሙቀት እንዲሁም የሰሜናዊ ህንድ ውቅያኖስ መደበኛ የባህር ወለል ሙቀት ሆኖ ሊቆይ እንደሚችል ትንበያዎች ይጠቁማሉ፡፡
በዚህም መሰረት በነሀሴና በመስከረም ወራቶችም የክረምት ዝናብ በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች ላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተገለፀ ሲሆን በዚህም መሰረት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት የሀገሪቱ አከባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸዉ በትንበያዉ ተጠቁሟል ።
የክረምት ወቅት ዝናብ አወጣጥም በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣እና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች የመዝግየት አዝማሚያ እንደሚኖር ተመላክቷል ፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ