ሐምሌ 28 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የአገርን የደን ሽፋን መጠን በማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን ተፅዕኖ ለመመከት እንደሚረዳ፣ የገቢ ምንጭ እና የስራ ዕድልም እንደሚፈጥር ባለሙያዎች ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ይህ መርሃ ግብር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ለጣቢያችን የገለፁት በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ መሪ ስራ አስፈጻሚ እና የአረንጓዴ ልማት አሻራ ብሄራዊ ኮሚቴ ዋና ጸሃፊ አቶ ፋኖሴ መኮንን ናቸው፡፡
በአገር ውስጥ ከሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ባለፈ፣ ጎረቤት ሀገራትም ይህንኑ ተግባር እንዲያከናውኑ ችግኞችን በመስጠት እና ልምድ በማጋራት ባለፉት ዓመታት የነበረውን ትስስር ማጠናከር እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ለተለያዩ ሀገራት ችግኞችን መስጠቷን በመጥቀስ ዘንድሮ የተሰጠ ችግኝ ባይኖርም ነገር ግን በሽያጭ ደረጃ ከሀገራቱ ጋር ትስስር መኖሩን ገልፀዋል፡፡
አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ የሚነሱ ወንዞች ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸው ወደ ጎረቤት ሀገራት ለም አፈር ሸርሽሮ የመውሰድ እና ጎርፍም የሚያስከትልበት ሁኔታ እንደነበረ በመጥቀስ አሁን ላይ እነኚህ ችግሮች እንዲቀንሱ ማስቻሉን አቶ ፋኖሴ ገልጸዋል፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ