ሐምሌ 21 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሁኔታ ወደ ጦርነት ያመራል በሚል በርካቶች አስተያየት እየሰጡ እንዳሉ ይታወቃል።
ከመንግስት ባለፈ ምሁራን እና ዲፕሎማቶች ሰላም እንዲሰፍን የመፍትሄ ሃሳብ በማቅረብ ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባ የዲፕሎማሲ እና የአለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያዎች ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት ባይኖራትም፤ ከኤርትራ በኩል የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ወደ ጦርነት የመግባት አዝማሚያ የሚታይበት በመሆኑ፣ በመንግስት ከሚወሰዱ እርምጃዎች ባለፈ ምሁራን ሰላምን ማስፈን የሚያስችል የመፍትሄ አማራጭ ማመላከት እንደሚገባቸው የገለፁት ዲፕሎማት እና የውጭ ግንኙነት ባለሙያ አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ናቸው፡፡
አሁን ላይ እየተፈጠረ ያለውን ሁኔታ ምሁራን ከስሜታዊነት ይልቅ በሰከነ መንገድ በመመልከት በተለያዩ አማራጮች ሃሳባቸውን ሲገልፁ ግጭት አባባሽ ከመሆን ይልቅ፣ መፍትሄ አመላካች ሃሳቦችን በማንሳት ሁለቱ ሀገራት በጋራ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችላቸውን መንገድ ማመላከት ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ይህንኑ ሃሳብ የሚያጠናክሩት በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ዲፕሎማሲ መምህር አቶ አበራ ሄብሶ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ዲፕሎማቶች፤ ኤንባሲዎች እንዲሁም ምሁራን በኢትዮጵያ እና ኤርትራ በኩል ያለውን የባህል፣ የቋንቋ እና ሌሎችም ትስስሮችን በማሳወቅ፤ ሰላም መፍጠር የሚያስችሉ ስራዎችን አጠናክረው ሊያሰሩ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
በኤርትራም በኩል ህዝቡ ሰላም ፈላጊ እንጂ ጦርነት ምርጫው ባለመሆኑ ኤርትራውያን ምሁራንን በተለያዩ አማራጮች በመጋበዝ የሰላም አንድ አካል እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ቀደምት ሉዓላዊት አገርነቷ የሚካድ ባለመሆኑ፤ ጫናዎች ሲፈጠሩ ምሁራን ውጥረት የሚያረግቡ የመፍትሄ ሃሳቦችን በማቅረብ ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባ ባለሙያዎቹ አፅንዖት ሰጥተውበታል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ