ሐምሌ 07 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)ምርጫ ቦርድ በስራ ላይ የሚገኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ስነ ምግባር አዋጅ 1162/2011 ላይ ማሻሻያ በማድረግ ለውይይት ያቀረበ ሲሆን፤ ፓርቲዎች ቦርዱ አዋጁን በተመለከተ በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን በመውሰድ ለማሻሻል መነሳሳቱ መልካም ቢሆንም፤ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ እጩዎች በምርጫ ጣቢያቸው የ3ሺህ ሰዎችን አዎንታ በፊርማ እንዲያቀርቡ የሚጠይቀው ላይ ማሻሻያ አለመደረጉ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
ቦርዱ ማሻሻያ ለማድረግ መነሳሳቱ መልካም ቢሆንም፤ በፓርቲዎች የሚሰጡ አስተያየቶችን ማካተት እንደሚገባ አፅኖት የሰጡት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ /ኢሶዴፓ/ ምክትል ዋና ሊቀመንበር ዶክተር ራሔል ባፌ፤ ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በረቂቅ አዋጁ ላይ ያላቸውን አስተያየት በጽሑፍ ማቅረባቸውን በማመላከት በተግባር ፓርቲዎችን አላሰራ ያሉ ጉዳዮች ትኩረት እንዲያገኙ መጠየቃቸውን አስታውቀዋል፡፡
የመንግስት ሰራተኛ ሁነው በምርጫ የሚሳተፉ ግለሰቦችን በተመለከተ በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎች በዚህኛው ረቂቅ አዋጅ መፍትሔ እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰው አሁንም የሚቀሩ ሃሳቦች እንዳሉና በተለይም እጩዎች ከምርጫ ጣቢያቸው የ3 ሺህ ሰዎችን ፊርማ እንዲያቀርቡ የሚጠይቀው አንቀጽ፤ ሴት እጩ እና አካል ጉዳተኞችን ለአካላዊና ለተለያዩ ጥቃቶች እየዳረገ መሆኑን በማመላከት በቀጣይ መሻሻል እንዳለበት አክለዋል፡፡
የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራርና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የምርጫና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ተሻሽለው የቀረቡ ሀሳቦች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ነገር ግን በቀጣይ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት ከእጩዎች ፊርማ ጋር የተገናኘው ድንጋጌ ተሻሽሎ ይቀርባል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
አዋጁ ምንም እንኳ እስካሁን በምርጫ ቦርድ በኩል ተግባራዊ ባይደረግም መውጣት ይገባው እንደነበርም አጽኖት በመስጠት በተለይ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሸነፉባቸው አከባቢዎች ያለው የዴሞክራሲ ሒደት መታየት እንደሚገባው በፓርቲዎች በኩል መነሳቱን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አላሰራ ያሉ አንዳንድ አንቀጾች እንዲሻሻሉ ፓርቲዎች ጠይቀዋል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ