ሐምሌ 04 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በሸዋሮቢት ከተማ፣ የ10 ዓመት ህፃንን “የመከላከያ ሰራዊት አባል ነኝ” በማለት አታልሎ 80 ኪሎ ግራም ጤፍ የሰረቀ ግለሰብ፣ በህብረተሰቡና በፖሊስ የተቀናጀ ጥረት ተይዞ በ5 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት መቀጣቱን የከተማው ፖሊስ ጽ/ቤት አስታወቀ።
የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመው ሐምሌ 01 ቀን 2017 ዓ.ም በሸዋሮቢት ከተማ ቀበሌ 03፣ “ሀይማ” በተባለ ልዩ ስፍራ ነው። ተከሳሽ አቶ አቡሽ ወርቅነህ ውቤ፣ የተበዳይ አቶ አሳልፈው ዘንባለው ቅጥር ግቢ ዘሎ በመግባት በወቅቱ ቤት ትጠብቅ የነበረችውን የ10 ዓመት ህፃን ልጅ ገጥሞታል።
የሸዋሮቢት ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት የወንጀል ታክቲክ ምርመራ ክፍል ኃላፊ ዋና ሳጅን ስንዴው አጥላው እንደገለጹት፣ ተከሳሹ ራሱን እንደ ፀጥታ ኃይል አስመስሎ “ቤት ልፈትሽ ነው፣ ብርና ስልክ ካለ አውጪ” በማለት ህፃኗን አስፈራርቷል። ህፃኗም በቤት ውስጥ ገንዘብና ስልክ እንደሌለ ስትነግረው፣ ግለሰቡ ቤቱን በመፈተሽ 14,400 ብር የሚገመት 80 ኪሎ ግራም ጤፍ ወስዷል።
ሌባው ጤፉን ተሸክሞ ከቤት ከወጣ በኋላ በጋሪ ጭኖ ሊሰወር ሲል፣ ድርጊቱን በንቃት ትከታተል የነበረችው ህፃን በፍጥነት ለጎረቤቶቿ ጥቆማ ሰጥታለች። ወዲያውኑ የደረሰው ህብረተሰብም ግለሰቡን በክትትል እጅ ከፍንጅ በመያዝ ለፖሊስ አስረክቧል።
ፖሊስም ፈጣን ምርመራ በማድረግ መዝገቡን ለዐቃቤ ህግ ልኳል። የሸዋሮቢት ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤትም ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው የተፋጠነ ችሎት፣ ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ “ወንጀለኛው እንዲታረምና ሌሎች ከድርጊቱ እንዲማሩ” ያለውን የ5 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት ቅጣት አስተላልፎበታል።
ዋና ሳጅን ስንዴው ወንጀልን በመከላከልና ወንጀለኞችን በማጋለጥ ረገድ ህብረተሰቡ ያሳየውን ተሳትፎ በማድነቅ፣ ይህ የተቀናጀ አሰራር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ