ሰኔ 30 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በአፋር ክልል በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ከመጠለያ ጣቢያ በማስወጣት ወደ ቀድሞ ቦታቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን በአፋር ክልል የገብር ዞን ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል።
ከታህሳስ ወር ጀምሮ በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ መኖሪያቸው ከመመለስ አስቀድሞ የተጎዱ መሰረት ልማቶችን የመገንባት ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
ነዋሪው ከመመለሱ አስቀድሞው ጥናት በማድረግ ምንም ስጋት አለመኖሩ የተረጋገጠ በመሆኑ ወደ ቀድሞው መኖሪያቸው እንዲመለሱ ስራዎች መጀመራቸውን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አብዱ አሌ ተናግረዋል።
ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርትና ጤና ተቋማት በመገንባት፣ ተፈናቃዮችንም ወደ መኖሪያ መንደራቸው በፍጥነት ለመመለስ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አክለዋል።
በሺ የሚቆጠሩ ዜጎች በመጠለያ ጣቢያ እንደሚገኙ በማንሳት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ነዋሪዎቹ ለ8 ወራት በመጠለያ ጣቢያ መቆየታቸውን የገለጹት አስተዳዳሪው፣ እስካሁን በመንግስት ድጋፍ ሲደረግላቸው እንደነበር አስታውቀው በቀጣይም ባሉበት እስኪቋቋሙ ድረስ ክትትል እንደሚደረግ አክለዋል።
ምላሽ ይስጡ