ሰኔ 30 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች ዘመናዊ የመንገድ ግንባታ እየተሰራ ቢሆንም፣ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ አለመሆኑን የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሄራዊ ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ድባቤ ባጫ ገልጸዋል፡፡
ለአካል ጉዳተኞች በድምፅ፣ በምስል እና በተለያዩ አማራጮች የተደገፉ ስራዎች እንደማይሰሩ አክለዋል።
በበጀት ዓመቱ በተደረገው የ6 ወራት ጥናት በመዲናዋ 3 ሴት አካል ጉዳተኛ የብሔራዊ ማህበሩ አባላት በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል፡፡
የዊልቸር ተጠቃሚዎችን ጨምሮ ለአይነ ስውራን በድምጽ፤ መስማት ለተሳናቸው ደግሞ በምስል የተደገፈ መረጃ በተለይ በዋና ዋና ማቋረጫ መንገዶች ላይ ባለመኖሩ ችግሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያባባሰው መሆኑንና ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ከመንገድ ደህንነት፤ ከመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ እና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር በጋራ የመስራት ክፍተት እንዳለ ያመላከቱት ስራ አስፈፃሚዋ፣ የደጋውን መጠን ለመቀነስ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።
የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አባሶ፣ አገልግሎቱ የትራፊክ አደጋ የሚበዛባቸው አካባቢዎችን በመለየት ከተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት ጋር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
አካል ጉዳተኞች በስፋት ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ እንደሆኑ ገልጸው፣ ዘመናዊ አሰራርን ከመዘርጋት አንጻር በትብብር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል በበጀት አመቱ በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስና ፍሰቱን ለማሳለጥ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ገልጿል፡፡
የቢሮው ሃላፊ ወ/ሮ እናታለም መለስ በበጀት አመቱ ሁሉንም የአካል ጉዳት አይነት ያማከለ 53 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መንገድ መገንባቱን አስታውቀዋል።
ይህም የአካል ጉዳተኞችን የትራፊክ አደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስ እንደሚረዳ ገልፀዋል፡፡
በሃገር አቀፍ ደረጃ በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን የሚያጡ ዜጎች ቁጥር በአመት ከ3 ሺህ እስከ 4ሺህ እንደሚደርስና በልዩነት ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ መስራት እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ