ሰኔ 24 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በህንድ ደቡባዊ ግዛት ቴልጋና በሚገኝ አንድ የመድኃኒት ፋብሪካ ውስጥ የኬሚካል ሬአክተር በመፈንዳቱ በተነሳ የእሳት አደጋ ቢያንስ 36 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች መቁሰላቸው ተዘግቧል፡፡ አደጋው የደረሰው ትናንት ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ ተገምቷል።
የአካባቢው ባለሥልጣናት እንደገለጹት፣ ፍንዳታው የተከሰተው በሲጋቺ ኢንዱስትሪዎች (Sigachi Industries) በተባለ ፋብሪካ ውስጥ ሲሆን፣ ፍንዳታውን ተከትሎ ከፍተኛ እሳት ተነስቷል ነው የተባለው። የእሳት አደጋ ሰራተኞች እና የነፍስ አድን ቡድኖች ወደ ስፍራው በመድረስ የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር እና ተጎጂዎችን ለማውጣት ጥረት ሲያደረጉ ታይተዋል ነው የተባለው።
አደጋው ሲከሰት ከ100 በላይ ሰራተኞች በፋብሪካው ውስጥ እንደነበሩ ተገልጿል። በርካታዎቹ አስከሬኖች ከመቃጠላቸው የተነሳ ማንነታቸውን ለማወቅ የዲኤንኤ ምርመራ እንደሚያስፈልግ የጤና ባለስልጣናት አስታውቀዋል። የቆሰሉ ሰዎች በአቅራቢያው ወደሚገኙ ሆስፒታሎች የተወሰዱ ሲሆን፣ የበርካቶቹ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ተነግሯል።
የፍንዳታው መንስኤ እስካሁን ባይታወቅም፣ ባለሥልጣናት የክስተቱን መንስኤ ለማጣራት ምርመራ መጀመራቸውን ገልጸዋል። በህንድ ውስጥ በፋብሪካዎች በተለይም በኬሚካል እና መድኃኒት ፋብሪካዎች ውስጥ የኢንዱስትሪ አደጋዎች የተለመዱ ናቸውም ተብሏል። ይህ አደጋ በፋብሪካዎች ውስጥ ያሉ የደህንነት መስፈርቶች እና ቁጥጥር ጥያቄ ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉ ተመላክቷል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ