ሰኔ 24 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል የሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የምክክር ሂደት ከመጀመሩ አስቀድሞ ከክልሉ ወጣቶች ጋር ልዩ የውይይት መድረኮች እንደሚኖሩ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታወቋል፡፡
የትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት በጦርነት ውስጥ በማለፉ እና አሁንም ከስብራትቱ ሙሉ በሙሉ ባለማገገሙ የክልሉ በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለተካዊ ጉዳዮች፣ በምክክር ሂደቱ በልዩነት የሚታይ መሆኑን ያነሱት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሸን ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ፣ በምክክር ሂደቱ በተለይ የክልሉ ወጣቶች ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት የምክክር ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት ከወጣቶች ጋር የተለያዩ የውይይት መድረኮች እንደሚዘጋጁ የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፣ በክልሉ የሚገኙ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር እንደሚደረገው ሁሉ፣ ወጣቶችም የራሳቸውን አጀንዳዎች እንዲሰጡ አስቻይ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ አመላክተዋል።
የክልሉ ወጣቶች ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የተሳተፉና ከፍተኛ የኑሮ ፈተናዎችን ያሳለፉ በመሆናቸው፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ወጣቶች በጦርነቱ ሳቢያ የደረሰባቸውን ስነ ልቦናዊ እና ማህበራዊ ተፅዕኖ ተገንዝቦ፣ በምክክሩ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ እንደ ትልቅ ግብዓት እንደሚወስደዉም ነው ያመላከቱት፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ወደ ተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች እና ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ በርካታ ወጣቶች እና የማህበረሰብ ክፍሎች መኖራቸውን የገለጹት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራር አቶ ጣዕመ አረዶም፣ በክልሉም ሆነ በጎረቤት ሀገራት በሚገኙ የተፈናቃይ መጠለያዎች፣ ለእያንዳንዱ መጠለያ ጣቢያ ተወካይ እንዳለው ይናገራሉ፡፡
በመሆኑም በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ የክልሉ ወጣቶች እና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳ እንዲያቀርቡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ምቹ ሁኔታዎችን እያመቻቸ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ይህም በጦርነቱ ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎች አጀንዳቸውን ለማካተት እና የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ለማስቻል ያለመ ነው ብለዋል፡፡ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮች ያጋጠሟቸውን ችግሮች፣ ስጋቶቻቸውን እና ለቀጣይ የሰላም ግንባታ እና እርቅ ሂደቶች ያላቸውን ሀሳብ ለምክክር ኮሚሽኑ እንዲያቀርቡ ከፌዴራሉ መንግስት ጋር ሰፋፊ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ነው ያመላከቱት፡፡
ወጣቶችን እንዲሁም ተፈናቃይ የማህበረሰብ ክፍሎችን በሀገራዊ ውይይት ውስጥ ማካተት ከጦርነቱ በኋላ ለሚኖረው የሰላም እና የመረጋጋት ግንባታ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ያስችላል ተብሎ እንሚጠበቅም ተመላክቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ