ሰኔ 16 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በቅርቡ በተደረገ ጥናት እስካሁን ካለው የህዝብ ቁጥር የዜሮ አምፖል ተጠቃሚዎችን ጨምሮ 63 በመቶ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ እንደሆነ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፕሮሰስና ኳሊቲ ማኔጅመንት ሃላፊው አቶ እሱባለው ጤናው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ 92 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆን ሃይል ከውሃ፣ እንዲሁም 98 በመቶ የሚሆን የኤልክትሪክ ሃይል ደግሞ ከታዳሽ ሃይል ኤሌክትሪክ እንደምታመነጭ የገለጹት ሃላፊው በአመት ውስጥም ወደ 7ሺህ 350 ሜጋ ዋት ሃይል በማመንጨት ከአፍሪካ 7ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ ከፍተኛ ቢሆንም ካለው የህዝብ ቁጥር አንጻር የተሰራው ስራ በሚጠበቀው ልክ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡
በሃገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተስፋፉ በሄዱ ቁጥር ከፍተኛ የሃይል መጠን እንደሚያስፈልግና ይህንንም ለማድረግ ተቋሙ ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በጋራ መስራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱ በአሁኑ ወቅት ከ20 ሺህ በላይ ሃገር አቋራጭ ታወሮች ያሉት ሲሆን በአብዛኛው አከባቢዎች ተቋሙ ሰራተኛ ቀጥሮ የሚያስጠብቃቸው ባለመሆኑ በተለያዩ አካላት ስርቆት እንደሚፈፀምና ለስራው ተግዳሮት እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከሃይል አቅራቢ ተቋሙ ጋር በጋራ በመሆን እስካሁን ድረስ 63 በመቶ ለሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ማዳረስ ቢቻልም 37 በመቶ የማህበረሰብ ክፍል ደግሞ ምንም የሃይል አገልግሎት እንደማያውቅ አመላክተዋል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ