ሰኔ 13 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ያልተሻሻሉ መስፈርቶች መኖራቸው የምግብ አምራች ተቋማትን ለመቆጣጠር እንቅፋት መፍጠሩን የገለጸው የአዲስ አበባ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ነው፡፡
ብዙዎቹ የምግብ አምራች ተቋማት የሚመሩት ከ10 አመታት በፊት በወጣ መስፈርት መሆኑንና የከተማው ምግብና መድሃኒት ባለስልጣንም ይህንኑ እየተጠቀመ እንደሚገኝ የገለጹት በአዲስ አበባ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ምግብና ጤና-ነክ ብቃት ማረጋገጥ ዳይሬክተር ወ/ሮ ቤዛዊት ግርማ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ብዙዎቹ ተቋማት ብቃት ማረጋገጥ እንዲችሉ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጥረት እያደረገ ቢገኝም ያልተሻሻሉ መስፈርቶች ለስራው እንቅፋት መፍጠራቸውን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። የደረጃ መቆጣጠሪያዎች ቢያንስ በየአምስት አመቱ መታደስ ይኖርባቸዋል ያሉት ወ/ሮ ቤዛዊት በቀጣይ አመት መስፈርቱን ለማሻሻል እቅድ መያዙን አንስተዋል፡፡
በአሁኑ ሰአት እየወጡ ያሉት የምግብ መስፈርቶች ብዙ በመሆናቸው ጉዳዩ ተጠንቶ ወደ ፌደራሉ ጥያቄ ሲቀርብ በጋራ ታይቶ የሚወሰን ይሆናል በማለት ጉዳዩ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣንን ብቻ ሳይሆን ደረጃዎች ኢንስቲትዮትንም የሚያካትት መሆኑን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ምግብ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ነጋሽ ስሜ የምግብ ደህንነት በደረጃና መርህ መሰረት ቁጥጥር መደረግ ስላለበት እንዲሻሻል መፈለጉ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
የምግብ ማምረቻና ማዘጋጃ አካባቢዎችን በተሻሻለ መስፈርት መቆጣጠር አንዱ የምግብ ደህንነትን ማስጠበቂያ መንገድ መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ ቤዛዊት ፡ተቋሙ የቀጣይ አመት ቀዳሚ ትኩረቱ እንደሚያደርገው አመላክተዋል።
ምላሽ ይስጡ