ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አከባቢዎች በህገወጥ መንገድ የቀንድ ከብት ንግድ ሲያከናውኑ የነበሩ ከ200 በላይ ነጋዴዎች ህጋዊ የንግድ ፍቃድ መውሰዳቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
በመዲናዋ የቀንድ ከብት ሽያጭ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚከናወን የሚገልፁት የቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ፍሰሃ ጥበቡ፤ ከዚህ ቀደም በስፋት ህገወጥ ሽያጭ ከሚከናወንባቸው የንግድ ቦታዎች አንዱ በነበረው የጉለሌ ሸጎሌ የንግድ ማዕከል 230 ነጋዴዎች ህጋዊ ፍቃድና የመለያ ባጅ ወስደው ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
በንግድ ቦታዎች የአሰራርና የቁጥጥር ለውጥ መደረጉን የተናገሩት ሃላፊው የንግድ ፍቃድና ባጅ የወሰዱ ነጋዴዎች፤ ከብቶቹን ለሚጭኑና ለሚያወርዱ እንዲሁም በጥበቃ ስራ ላይ ለተሰማሩ አባላት እንደየድርሻቸው የመለያ ዩኒፎርም እየተዘጋጀ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
በቀጣይ በየካ፤ አቃቂ እና ላፍቶ ክፍለ ከተማ በሚገኙ የቀንድ ከብት የንግድ ቦታዎች የመለያ ባጅ እንደሚሰጥ ያስታወቁት ኃላፊው ብርጭቆ ተብሎ በሚጠራበት ሰፈር የሚገኘውን የፍየልና በግ ገበያ እንደሚያካትት ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይም ህገወጥ ደላሎች ሸማች በመምሰል በንግዱ እንቅስቃሴ እንደሚሳተፉ የተናገሩት አቶ ፍሰሃ፤ በንግድ ስፍራዎቹ የህግ አስከባሪ አካላት የሚገኙ በመሆኑ ነጋዴውም ሸማቹም በአቅራቢያው ለሚያገኝ ተቆጣጣሪ በማሳወቅ ሃላፊነቱ እንዲወጣ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ