ከጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ ተነስቶ ወደ አሜሪካዋ ግዛት ቴክሳስ በመጓዝ ላይ ያለ አውሮፕላን ውስጥ አንድ ተሳፋሪ የአውራፕላኑን በር ለመክፈት በመሞከሩ በረራው ተቋረጠ።
አውሮፕላኑ በድንገተኛ ሁኔታ በረራውን አቋርጦ አሜሪካ ውስጥ ሲያትል እንዲያርፍ ተገዷል። የጃፓን አየር መንገድ አውሮፕላን በጉዞ ላይ ሳለ “በአስቸጋሪ ተሳፋሪ” ምክንያት በድንገት እንዲያርፍ መወሰኑም ተገልጿል።
የአውሮፕላኑ ባለቤት ኦል ኒፖን አየር መንገድ እንዳለው የበረራ ቁጥር 114 ከመዳረሻው ውጪ ወደ ሲያትል ጉዞውን እንዲያደርግ ተገዷል። የሲያትል ፖሊስም የአውሮፕላን በር ለመክፈት የሞከረ ተሳፋሪ እንደነበር ጥቆማ ደርሶታል።
“በበረራ ወቅት የአውሮፕላኑን በር ለመክፈት ተሳፋሪው ሞክሯል” ብሏል። ማንነቱ ያልተገለጸው ግለሰብ “የጤና ቀውስ ውስጥ እንደገባ” ከዚያም በሌሎች ተሳፋሪዎች እና የበረራ መስተንግዶ ባለሙያዎች በሩን እንዳይከፍት እንዳስቆሙት በፖሊስ ተገልጿል።
ግለሰቡ አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላ ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን፣ ክስ የሚመሠረትበት ስለመሆኑ ግን የታወቀ ነገር የለም። አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ “የተሳፋሪዎች እና የበረራ አስተናጋጆች ደኅንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው። የአካባቢው ፖሊስ ላደረገልን ድጋፍ እናመሰግናለን” ብሏል።
አውሮፕላኑ በሲያትል፣ ታኮማ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲያርፍ ከተደረገ በኋላ በድጋሚ ለመብረር እየተጠባበቀ ሳለ ሌላ መንገደኛ “አስቸጋሪ ባህሪ” በማሳያቱ ከአውሮፕላኑ እንዲወጣ ተደርጓል። አውሮፕላኑ ከተያዘለት ጊዜ አራት ሰዓት ዘግይቶ በሂውስተን፣ ጆርጅ ቡሽ አህጉር አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሷል።
ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ክስተቶች ተዘግበዋል። ከወራት በፊት ከኢንዶኔዢያ፣ ባሊ የተነሳ አውሮፕላን ወደ ሜልበርን፣ አውስትራሊያ እየተጓዘ ሳለ አንድ ተሳፋሪ በር ለመክፈት በመሞከሩ በረራው ተቋርጧል።
ከዚያ በፊት ደግሞ የአሜሪካ አውሮፕላን ውስጥ በር ለመክፈት የሞከረን ግለሰብ በፕላስተር በማሰር ከድርጊቱ ማስቆም ተችሏል። ባለፈው ዓመት የኤዥያን አየር መንገድ ተሳፋሪ የአውሮፕላኑን የአደጋ ጊዜ በር መክፈቱን ተከትሎ ዘጠኝ ሰዎች ተጎድተው ሆስፒታል መግባታቸው ይታወሳል።
ቢቢሲ
ምላሽ ይስጡ