የአሜሪካ እና የደቡብ አፍሪካ ግንኙነት ወደ መሻከር ከመሄዱ በፊት ተወያይቶ ለማስተካከል ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሳ ወደ አሜሪካ ማቅናታቸዉ ይታወቃል፡፡
በቀጥታ ስርጭት በሚተላለፍ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በደቡብ አፍሪካ “የነጮች ዘር ማጥፋት” እየተካሄደ ነው የሚሉ ክሶችን ዶናልድ ትራንፕ በማንሳት ራማፎሳን ሲያስደነግጧቸዉ ታይቷል።
ትራምፕ በርካታ የመቃብር ስፍራ ላይ ያሉ መስቀሎች የታዩበትን ምስል ለራማፎሳ በማሳየት፣ እነዚህም የተገደሉ ነጭ ገበሬዎች የመቃብር ስፍራዎች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ፕሬዘዳንቱ የትኞቹ እንደሆኑ አላዉቅም ነገር ግን እነዚህ መስቀሎች እውነተኛ መቃብሮች ሳይሆኑ፣ በ2020 በኳዙሉ-ናታል ግዛት በአንድ እርሻ ቦታ ባልና ሚስት ከተገደሉ በኋላ በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የታዩ ይመስላሉ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከዚህ ስብሰባ በፊት ራማፎሳ ከአሜሪካ ጋር የንግድ ግንኙነት ማሻሻል ቀዳሚ ተግባራቸው እንደሆነ ገልጸው ነበር ነገር ግን ስምምነትን የሚያሳዩ ንግግሮች ከትራንፕ አልተደመጡም።
ትራምፕ የነጮች ዘር ማጥፋት በሚመለከት “ማብራሪያ” እንደሚያስፈልጋቸው ሲናገሩ፣ ራማፎሳ መንግስታቸው ለእንደዚህ አይነት ነገሮች ቦታ እንደሌለው ገልጸዋል። ይህን ለማሳየትም አብረዋቸዉ ያሉ ሶስት ነጭ ልኡካንን እየጠቆሙ የዘር ማጥፊት ቢኖር ኖሮ እነዚህ ሰዎች ዛሬ እዚህ አይገኙም ነበር ብለዋል።
ትራንፕ ማዋከባቸዉን ቀጥለዉ ተቃዋሚዉ ጁሊየስ ማሌማ በነጮች ዙሪያ የተናገረዉን የንግግር ቪዲዮ ማብራሪያ እንዲሰጡበት ጠይቀዋል ራማፎሳ በበኩላቸዉ ይህ የሙዚቃ ቪዲዮ የመንግስት ፖሊሲ አይደለም፣ በደብብ አፍሪካ የመድብለ ፓርቲና ዴሞክራሲ አለን ሲሉ ተናግረዋል።
አንድ ጋዜጠኛ ነጭ ገበሬዎች ደቡብ አፍሪካን ለቀው ቢወጡ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ሲጠይቅ ራማፎሳ ጥያቄውን ለነጭ የግብርና ሚኒስትራቸው ለጆን ስቴንሁይሰን በማስተላለፋቸው ብዙ ገበሬዎች መቆየት ይፈልጋሉ የሚል ምላሽ ሚኒስትሩ መስጠታቸዉን ቢቢሲ ዘግቧል።
__
ምላሽ ይስጡ