የሕግ፣ የነጻነትና የገለልተኝነት ጥያቄዎች የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ለምክክር ኮሚሽኑ የሚያቀርባቸው ቁልፍ አጀንዳዎች መሆን እንዳለባቸው ለመናኸሪያ ሬዲዮ ሃሳባቸውን ያሳፈሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ሀገር ልትመክርባቸውና መፍትሄ ልታመጣባቸው ከሚገቡ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትና የገለልተኝነት ጉዳይ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያው ጋዜጠኛ ቦጋለ ተስፋዬ ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙሃን የአራተኛ መንግስትነት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ከጫና እና ከተጽእኖ የተላቀቁ መሆን እንደሚገባቸው የሚገልጹት ጋዜጠኛ ቦጋለ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዘርፉ እየተዳከመ መምጣቱንና በማህበራዊ እና በዲጂታል መገናኛ ብዙሃን እየተበለጠ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የሃሳብ ነጻነት በተግባር ሊረጋገጥ የሚችለው በመገናኛ ብዙሃን መሆኑን ገልጸው፤ ይህን ለማስተግበር ከወዲሁ እንደ ሀገር የምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳ አድርጎ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የሚወጡ ህግና ደንቦችም የመገናኛ ብዙሃንን ገለልተኝነትና የሃሳብ ነጻነት የሚጋፉ እንዳይሆኑ መሞገት ተገቢ መሆኑን ባለሙያው ጠቅሰዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የሙያ ስነ-ምግባርን የሚያስጠበቅ፤ ነጻነትና ገለልተኝነትን የሚያስከብር የሕግ ማእቀፍ እንዲኖር አጀንዳ አድርገው ለኮሚሽኑ ማቅረብ እንደሚገባቸው ሌላኛው የዘርፉ ባለሙያ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ገልጸዋል።
በዘርፉ ሊሰማሩ የሚፈልጉ በርካታ አካላት ቢኖሩም ያሉት ህግና አሰራሮች በሚፈለገው ልክ አመቺ ባለመሆናቸው ብዙዎች ዘርፉን እየራቁ ነው ያሉት ጋዜጠኛው፤ የጠራ ሃሳብ በነጻነት እንዲንሸራሸር ለማድረግና ዘርፉ የአራተኛ መንግስትነት ሚናውን እንዲወጣ መገናኛ ብዙሃኑ የጋራ ጠንቃራ አቋምና አጀንዳ ሊያነሱ ይገባል ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃን ነጻና ገለልተኛ ሆነው መስራታቸው የሚጠቅመው ሀገርን ነው ሲሉ ያከሉት ጋዜጠኛ ጥበቡ ዘርፉ ሊከበርና ሊደገፍ እንጂ ምንም ሳይሰራበት ሊፈራ እንደማይገባው አክለዋል።
ሀገር በሃሳብ ልዕልና እና ነጻነት እንድታድግ የመገናኛ ብዙሃን ነጻና ገለልተኛ ሆኖ መስራት ላቅ ያለ ሚና እንዳለው ባለሙያዎቹ አመላክተዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ አጀንዳ ለመሰብሰብ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
የቀጥታ ስርጭት 👉 https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv
Telegram 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ