መናኸሪያ ሬዲዮ ያነጋገራቸው የኢንተርናሽናል ዲያስፖራ ፎረም ፕሬዝዳንት አቶ እንድሪስ መሃመድ፤ ለውጡን ተከትሎ ዲያስፖራው ማህበረሰብ በአገሩ ጉዳይ በተለያዩ ዘርፎች እንዲሳተፍ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲደረግለት ነበር ብለዋል፡፡
ከለውጡ በኋላ ከዲያስፖራው ማህበረሰብ የሚገኘው የሬሚታንስ ገቢ ጭማሪ ያሳየ ቢሆንም በአንዳንድ አከባቢዎች በሚታየው ግጭት ምክንያት አሁን ላይ ገቢው መቀዛቀዝ እያሳየ ነው ብለዋል።
በተለይም በአማራ እና በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እንዲሁም ከዚህ ቀደም የነበረው የሰሜኑ ጦርነት ተግዳሮት እንደፈጠረ አስረድተዋል፡፡
መሰል የጸጥታ ችግሮች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ትውልደ ኢትዮጵያን ቁጥር እንዲቀንስ አድርጓል የሚሉት ፕሬዚደንቱ፤ በየተቋማቱ የሚታዩ ቢሮክራሲዎችም ገፊ መሆናቸውን አክለዋል፡፡
ፕሬዚደንቱ ባለፉት ጊዜያት ከዲያስፖራው ማህበረሰብ የሚገኘው የሬሚታንስ ገቢ መቀዛቀዝ እየታየበት መሆኑን ገልጸው፤ በቅርቡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውጭ ሀገር ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችለውን ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤት ማቅረቡ ተገቢ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የሬሚታንስ ገቢ መጠንን ሊያሳድግ እንደሚችልም ነው ያመላከቱት፡፡
በዉጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊና ትዉልደ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ፤ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል።
በዛሬው እለት በሚደረገው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ምክር ቤቱ የውጪ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀሰ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የሚቀርብ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እንደሚመራ ይጠበቃል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
የቀጥታ ስርጭት – https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv
Telegram 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ