የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ እንዳስታወቀው ፍቃድ የተሰጣቸው እና እውቅና ያላቸው የሂሳብ እና የኦዲት ባለሙያዎች ከ1ሺህ 400 እንደማይበልጡ አረጋግጫለሁ ሲል ለጣቢያችን አስታውቋል፡፡
የቦርዱ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር ሀገሪቱ ያላትን የሂሳብ ባለሙያዎች ውስን መሆኑን ተከትሎ በዘርፉ ላይ የማጭበርበር እና ህጋዊ የሆነ ሰውነት የሌላቸው ባለሙያዎች ቁጥር ከፍ እንዲል እያደረገው ስለመምጣቱ ተናግረዋል፡፡ ቦርዱ እስካሁን በቆይታው 200 የሚጠጉ የሂሳብ አዋቂዎችን እንዲሁም 1ሺህ 200 የሚሆኑ የኦዲት ባለሙያዎች እውቅና እና ፈቃድ መስጠት ስለመቻሉ ነው ያስታወቁት፡፡
አክለውም ቦርዱ በሚያደርጋቸው ቅኝቶች በርካታ ችግሮችን እየተመለከተ ስለመሆኑ አስታውቀው፤በዚህም በተቻለ መልኩ የባለሙያዎችን ቁጥር የማሳደግ፤የቁጥጥር ስራን የማጠናከር እና አዳዲስ አሰራሮችን የመዘርጋት ተግባር ላይ ተሳታፊ እንደሚሆንም ነው ያመላከቱት፡፡
አያይዘውም በዘርፉ ያለውን ግድፈት መቆጣጠር የሚችል አካል በስፋት ባለመኖሩ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንዳሉ ጠቅሰው፤በዚህም ቦርዱ ፍቃዳቸውን የመንጠቅ እና በወንጀል ህጉ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራዎች ይሰራል ብለዋል፡፡ከዛም ባለፈ ቦርዱ ወደ ህጋዊ መስመር ማስገባት የሚቻልባቸዉን አካሄዶችን ይፈጥራልም ብለዋል፡፡
አሁንም ድረስ በሀገሪቱ ባሉ ክፍሎች በኩል የሂሳብ አዋቂ በማለት ራሳቸውን ሰይመው የሚንቀሳቀሱ አካላት እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን አስፈላጊውን ጥንቃቄ መወሰድ እንደሚገባም የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ አስታውቋል፡፡
ምላሽ ይስጡ