በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን፣ በከታማዋ ያሉ ተማሪዎች ስራ ላይ ሊውሉ የሚችሉ በርካታ የሳይንስ እና የፈጠራ ውጤቶችን ማቅረባቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልጿል፡፡
በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ያቀረቧቸው አብዛኞቹ የፈጠራ ውጤቶች ወደ ተግባር ተቀይረው ስራ ላይ ሊወሉ እና ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ መሆናቸውን የሚናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዲናኦል ጫላ ናቸው፡፡
ተማሪዎቹ የሰሯቸው የሳይንስ እና ፈጠራ ውጤቶች ለውድድር እና ለእይታ ብቻ ቀርበው በተማሪዎቹ እጅ መቅረት እንደሌለባቸውም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የፈጠራ ሰራዎች ተማሪዎች ጋር እንዳይቀሩ እንዲሁም ሀገር እና ህዝብን እንዲጠቅሙ ለማድረግ፣ ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
ይህ ብቻም ሳይሆን ተማሪዎቹ የሰሩትን የፈጠራ ስራ ለማህበረሰቡ እንዲያቀርቡ እና እንዲያስተዋዉቁ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እንደሚመቻችላቸውም ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በከተማዋ በሳይንስ እና ፈጠራ የታየው ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረው፣ በሁሉም ከፍለ ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ አክለው ገልጸዋል፡፡
በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከወትሮ በተለየ የትምህርት ዘመኑ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን በሳይንስ እና ፈጠራ እንዲሳተፉ መደረጉ በዘርፉ ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስገኘቱን ቢሮው መግለጹ አይዘነጋም፡፡
ምላሽ ይስጡ