ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በሰራችሁ ስራ ከዓለም አቀፍ ተቋማት እውቅና ማግኘቷን የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
ምንም እንኳን አሁንም የትራፊክ አደጋ በየቀኑ ከ9 ያላነሱ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ፤ አንዳንዴም በአንድ አደጋ ከ60 እስከ 20 ሰዎችን ሕይወት እየነጠቀ አሳሳቢ ሆኖ ቢቀጥልም፤ ባለፉት አመታት በተወሰነ መልኩ የሟቾች ቁጥር መቀነሱን መረጃዎች እንደሚያመላክቱ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አባሶ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከዓለም አቀፍ ተቋማት እውቅና ማግኘት መቻሉንና አሁንም የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ገልጸው፣በሰፊው ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት እንደሆነ አስታውቀዋል።
በትራፊክ አደጋ ምክንያት ህይወታቸው የሚያልፉ ዜጎች ቁጥር እየቀነሰ ነው ቢባልም፣ አሁን ላይ በሀገሪቱ ካለው ውስን የተሽካርካሪ ቁጥር አንፃር ከፍተኛ ስራ የሚፈልግ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ከዚህ በፊት በዓመት ከ5 ሺህ በላይ የሞት ምጣኔ ይመዘገብ ከነበረበት አሁን ላይ ወደ 3ሺህ 116 ዝቅ ማድረግ የተቻለ ቢሆንም ከዚህም በላይ መስራት እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ጋር በመሆን በተደጋጋሚ አደጋ የሚያጋጥምባቸው ቦታዎችን በመለየት የመንገድ ጥገና ስራ እየተከናወነ መሆኑን የመንገድ ደህንነትና ትምህርትና አቅም ግንባታ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዮሐንስ ለማ ገልጸዋል።
በቫይታል ስትራቴጂ የመንገድ ደህንነት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና ተጠሪ ኢንጂነር ዳንኤል ሞላ በበኩላቸው የትራፊክ አደጋዎች እንዲቀንሱ ጥናቶችን በማጥናት ምክረ ሃሳቦችን ለባለድርሻ አካላት በማቅረብ በተሰራው ስራ አዎንታዊ ውጤት መታየቱን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ሁሉንም አካላት በማስተባበር ከፍተኛ ንቅናቄ ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ምላሽ ይስጡ