በትራንዚት ጉዞ እና ኢትዮጵያ ዉስጥ በሚኖራቸዉ ቆይታ በተለያዩ የወንጀል ድርጊት ዉስጥ የተገኙ የዉጭ ሃገራት ዜጎች በኢትዮጵያ ህግ መሰረት ፍርድ ቤት ቀርበዉ ጥፋተኛ ሆነዉ ሲገኙ ፍርድ ተቀብለዉ በየማረሚያ ቤቱ እንደሚቆዩ ይታወቃል፡፡
ከባህል፤ከቋንቋና አመጋገብ ጋር ተያይዞ ታረሚ በሆኑባቸዉ ቦታዎች እንደሚቸገሩ እና ከቤተሰብ በመራቃቸዉ በተደጋጋሚ ዝዉዉር የሚጠይቁ ታራሚዎች መኖራቸዉ ይገለጻል፡፡
በሀገራችው የእስር ጊዜቸውን እንዲከታተሉ ከማደረግ አንጻር ብሎም የማረሚያ ቤቶች መጨናነቅን ከመቅረፍ አንጻር ምን ተሰርቷል ሲል መናኸሪያ ሬዲዮ ፍትህ ሚኒስቴርን ጠይቋል፡፡
በፍትህ ሚኒስትር በህግ ጉዳዮች አለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ የሱፍ ቢጃማው በሰጡት ምላሽ ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር እስረኞችን መቀያየር ብሎም የእስር ጊዜቸውን በትውልድ ሀገራቸው እንዲከታተሉ ማድረግ የሚያስችል ስምምነት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከሁለት ሀገራት ጋር ግን ያልጸደቀ ስምምነት መኖሩን አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር ባላት መልካም በሚባል የዲፕሎማያዊ ግንኙነት ባሳለፍነው ዓመት አሳልፋ የሰጠቻቸው ታራሚዎች እንዳሉ በመጥቀስ አሁንም ወደ 29 የሚጠጉ የብራዚል ሀገር ዜግነት ያላቸው ታራሚዎች በሀገራቸው የእስር ጊዜቸውን እንዲከታተሉ ጥያቄ አቅርበው እየታየ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለዉም እንደ ወንጀላቸው መጠን የእስር ጊዜቸውን ሲጨርሱ ዳግም ወደ ሀገሪትዋ እንዳይገቡ የማድረግ ስራ እንደሚስራም አመላክተዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ