የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካርድ ክፍያ ሥርዓቱን አንድ ደረጃ ከፍ ያደርጋል የተባለለትና በበይነ መረብ መጠቀም የሚያስችል ቨርቿል ማስተር ካርድን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።
ደህንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ ዓለም አቀፍ ዲጂታል ክፍያዎችን በቨርቹዋል ካርድ መጠቀም የሚያስችል መሆኑን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የንግድ ባንክ አገልግሎት ከሚጠቀመው አጠቃላይ ደንበኛ 85 በመቶ የሚሆነው የኦንላይን ባንኪንግ የሚጠቀምበት ደረጃ ላይ መድረሱን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ከ40 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የባንኩ ደንበኞች አገልግሎቱን ለማስጀመር ከማስተር ካርድ ጋር የተሰራው ሥራ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚያስገኝ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየሰራ ያለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን እና አካታች የኢኮኖሚ ዕድገትን ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጥምረት ለመስራት ያደረገውን ሥራ ያደነቁት የማስተር ካርድ የአፍሪካ ፕሬዝዳንት ማርክ ኤሊየት ዲጂታል የክፍያ አማራጮችን በማቅረብ፣ ንግድ ባንክ እና ማስተር ካርድ በፋይናንሺያል አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ያለውን ክፍተት ለመቅረፍ፣ የላቀ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎን እና የፋይናንስ አካታችነትን ለማጎልበት የታለመ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ