ባለፉት ጊዜያት ምክር ቤቱ በሀገራዊ የፖለቲካ፤ ማህበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያወጣቸው የአቋም ሪፖርቶች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡
ሆኖም ዛሬ ላይ ምክር ቤቱ በስም ብቻ ያለ ነገር ግን በአግባቡ ኃላፊነቱን መወጣት የማይችልበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ ምክር ቤቱ እንዲቋቋም ዋነኛ ምክንያቶች ከነበሩት ውስጥ የሚፈጠሩ የሃሳብ ልዩነቶችን በማስቀረት፤ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት እና ማጠናከር ዋነኛ አላማው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የቃል ኪዳን ሰነዶችን በማዘጋጀት በሀገሪቱ በሚከሰቱ ግጭቶች፤ በመንግስት፤ በህዝብ እንዲሁም በታጣቂ ሃይሎች በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን ተከታትሎ መግለጫ የማውጣት እና ውትወታ የማድረግ ስራ ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ሆኖም ዛሬ ላይ ምክር ቤቱ ከተጽዕኖ ፈጣሪነት ወደ የስም ተቋምነት ተቀይሯል ያሉት ዶክተር ራሔል፤ በምክር ቤቱ ላይ እየተፈጠሩ ባሉ ጫናዎች ምክንያት ተዳክሟልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በጋራ ምክር ቤቱ ላይ አስተዳደራዊ ተጽዕኖዎች መፈጠራቸው እና ዲሞክራሲያዊ የሆኑ ምርጫዎች አለመካሄዳቸው ችግር ፈጥሯል ብለዋል፡፡
ሌላኛው የጋራ ምክር ቤት አባል እና የኢህአፓ ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ሃይማኖት የጋራ ምክር ቤቱ አስፈላጊነት ግልጽ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተጣለበትን ሃላፊነት ወደ ጎን ትቶታል ብለዋል፡፡
ለአብነት የጋራ ምክር ቤቱ በሀገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችን፤ የኑሮ ውድነትን እና መሰል ችግሮችን በተመለከተ ምንም እያለ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ የአመራር ለውጥ ባደረገበት ወቅት ፓርቲያቸውን ጨምሮ ሌሎች 6 ፓርቲዎች እንዳልተገኙበት እና በስልጣን ላይ ያሉ አመራሮችንም እንደማይደግፍ ገልጸዋል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ የተቋቋመበትን ዓላማ በአግባቡ ከመወጣትም ባለፈ ራሱን ዳግም ማጤን ሊኖርበት እንደሚገባ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች አስታውቀዋል፡፡
መናኸሪያ ሬዲዮ በጉዳዩ ዙሪያ ምክር ቤቱን በተደጋጋሚ ለማነጋጋር ጥረት ቢያደርግም ምላሽ ሊሰጠን አልቻለም፡፡
ምላሽ ይስጡ