መጋቢት 17 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በቀይ ባህር ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቱ እየጨመረ በመምጣቱ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በምትከተለው መርህ የቀጠናው ውስብስብ የፖለቲካ ሁኔታ፤ ያላት ተደማጭነት እና አቋሟን በጥንቃቄ መምራት እንደሚገባ የአለም አቀፍ ግንኙነት ተንታኞች ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገለጸዋል።
የአለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ጥላሁን ሊበን፣ በቀይ ባህር ጉዳይ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በትብብር ላይ የተመሰረተ፤ ሰላማዊ በሆነ የጥቅም ማስከበር መሆን እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ከሃያላን ሀገራት ጋር ስትራቴጂካዊ ሽርክና መፍጠር ተገቢ መሆኑንም አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ በታሪክ የባህር በር መዳረሻ እንደነበራት በማስታወስ፣ አሁን ያለውን ወደብ አልባ ሁኔታ ለመለወጥ የምታደርገውን ጥረት በአለም አቀፍ ህግ መሰረት በዲፕሎማሲ መንገድ መምራት እንደሚገባት ይጠቅሳሉ።
በተለይም ከሃያላን ሀገራት ድጋፍ በሚፈለግበት ወቅት ብሄራዊ ጥቅምን ማስከበር እና ውስጣዊ አንድነትን መጠበቅ ቀጠናዊ ሰላምን ማረጋገጫ ወሳኝ ጉዳይ መሆን ባለሙያው ተናግረዋል።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ አበራ ሄጲሶ፣ መንግስታዊ ስምምነቶች የህዝብን ጥቅም ማስቀደም እንዳለባቸው ያነሳሉ።
ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚደረጉ ትብብሮችም የኢትዮጵያን አጠቃላይ ውስጣዊ እና ውጫዊ ዲፕሎማሲያዊ ስትራቴጂ እንዳያሻክሩ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት የሚያነሱት መምህሩ ካለፉ ስህተቶች በመማር፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር እና ሰላማዊ መፍትሄዎችን መፈለግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በቀይ ባህር ጉዳይ የኢትዮጵያ አቋም በጠንካራ ዲፕሎማሲ፣ በትብብር እና በውስጣዊ መግባባት የተመሰረተ መሆን እንዳለበት እና ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚደረጉ ትብብሮች አጠቃላይ የዲፕሎማሲ ስትራቴጂውን እንዳያደናቅፍ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተንታኞቹ አሳስበዋል።
ምላሽ ይስጡ