የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞ የከተማዋ ከንቲባ ጸጋዬ ቱኬ በ13 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አሳለፈ።
የከተማዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሌሎች ተከሳሾች ላይም የቅጣት ውሳኔውን አሳልፏል።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው ወንጀሉን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 17 ንዑስ 2 እና አንቀጽ 9 ንዑስ 2 በተደነገገው መሰረት ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ነው።
በዚህም አንደኛ ተከሳሽ የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጸጋዬ ቱኬ በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ ጥፋተኛ በመባላቸው የ13 ዓመት ጽኑ እስራትና የ21 ሺህ ብር ቅጣት ተወስኖባቸዋል።
ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ተሰማ ዳንጉሼ በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል የሦስት ዓመት ጽኑ እስራትና 1 ሺህ ብር የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
በተጨማሪም ሦስተኛ ተከሳሽ አቶ ታሪኩ ታመነ በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል 10 ዓመት ጽኑ እስራትና 41ሺህ ብር እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
እንዲሁም 4ኛ ተከሳሽ አቶ ታፈሰ ቱናሻ እና 5ኛ ተከሳሽ አቶ ሰይፉ ዴሊሳ እያንዳንዳቸው በስምንት ዓመት ጽኑ እስራትና በቅደም ተከተላቸው 51 እና 76 ሺህ ብር እንዲቀጡ የቅጣት ውሳኔ መሰጠቱን ኢዜአ ዘግቧል።
ምላሽ ይስጡ