በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ተቀጥሮ ሲሰራ ከተለያዩ የክፍያ አይነቶች የተሰበሰበ ገንዘብን ለግል ጥቅሙ አውሏል የተባለው ግለሰብ በጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጣቱ ተነግሯል፡፡
ተከሳሽ ዳንኤል አስራት ወ/ማርያም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 887 አንቀጽ 31 (1) አና (2) ስር የተመለከተውን የሕግ ድንጋጌ በመተላለፍ ከባድ የእምነት ማጉደል ወንጀል መፈጸሙ በክሱ ተመላክቷል፡፡
ተከሳሹ በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት አዲስ አበባ ፖስታ ቤቶች ጽ/ቤት ጎተራ ቅርንጫፍ ፖስታል ክለርክ ሆኖ ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም እስከ የካቲት 15 ቀን 2013 ዓ.ም በሰራበት ወቅት በተለያዩ የክፍያ አይነቶች ከተሰበሰበ ገንዘብ ውስጥ 204 ሺህ 687 ብር ለግል ጥቅሙ በማዋል ከባድ የእምነት ማጉደል ወንጀል መፈጸሙ ተጠቅሷል፡፡
በዚህም ተከሳሹ በሌለበት ክሱ ሲታይ የቆየ ሲሆን፤ዓቃቤ ሕግ ባቀረባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ወንጀል መፈጸሙን አረጋግጧል፡፡
በሌላ በኩል ተከሳሹ በመጥሪያ እንዲሁም በጋዜጣ ችሎት ላይ እንዲቀርብ ጥሪ ቢደረግለትም ባለመቅረቡ የመከላከል መብቱ ታልፎ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጥቶበታል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን የቅጣት ውሳኔ የተመለከተው የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ከባድ የሙስና ወንጀል ችሎት ዛሬ ባዋለው ችሎት ተከሳሹን በ2 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራትና በ7 ሺህ ብር እንዲቀጣ ወስኗል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ተከሳሹን አድኖ በመያዝ ለፌደራል ማረሚያ ቤት እንዲያስረክብም ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡
በተጨማሪም ለኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ተከሳሹ ከሀገር ሲወጣ ይሁን፤ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ ከተገኘ ለፌዴራል ፖሊስ እንዲያሳውቅ ትዕዛዝ ተስጥቷል ሲል ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል፡፡
ምላሽ ይስጡ