በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተከናወነው የሰላም ስምምነት ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለው እሳቤ በተግባር የተረጋገጠበት መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡
በ38ኛዉ የአፍርካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይም የኢትዮጵያ መንግስት በሃገሪቱ የነበረዉን ችግር ህብረቱ መፍትሄ እንዲሰጥበት ማድረጉ የሚደነቅ ተግባር እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ ይህ ስምምነት በወረቀት ላይ ብቻ ሰፍሮ እንዳይቀር ፤በስምምነቱ የተቀመጡ ነጥቦች እንዴት ሊተገበሩ ይገባል የሚለዉን መናኸሪያ ሬዲዮ ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና የአለማቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አብዱ አህመድ በትግራይ ክልል የነበረውን ግጭት ያስቆመውን የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ዘላቂ መፍትሄን ማምጣት ያልተቻለዉ ፖለቲካውን እየዘወሩት ያሉት ግለሰቦች፤ ከህዝባዊነት ይልቅ ድርጅታዊ እሳቤ ላይ ትኩረት በማድረግ ስለተጠመዱ ነው ፤ ይሄ ደግሞ እንደሃገር አሳዛኝ የታሪካችን ገጽ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱ በአንድ በኩል በሃገሪቱ የነበረውን አስከፊ ጦርነትና እልቂት የቋጨና ሰዎች በሰላም መግባት መውጣት እንዲችሉ ያደረገ ቢሆንም በሌላ በኩል ግን መሄድ በነበረበት ልክ አለመጓዙ አፈጻጸሙ ላይ ክፍተት በመታየቱ በዜጎች የሚነሱ ቅሬታዎች በርትተዉ እንዲታዩ አድርጓል ብለዋል፡፡ ትግራይ ክልል ዉስጥ ያሉ የተለያዩ አደረጃጀቶችና የፌደራል መንግስት፤ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ መስራትና የስምምነቱ አንቀጾች ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ማድረግ እንዳለባቸዉ አሳስበዋል፡፡
ሌላኛው የስነ-አመራርና የፖለቲካ መምህር አቶ ጌትዬ ትርፌ በበኩላቸው ለፕሪቶሪያው ሰምምነት ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ አለመሆን እንደ እንቅፋት የሆኑ በርካታ ነገሮች አሉ ፤ በተለይም የውጪና የውስጥ ጣልቃገብነት መስተዋሉ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አፈጻጸሙን ለማሻሻል የሃሳብ ልዩነትን ሳይሆን የስልጣን ሽሚያን መቀነስ፤ የቃላት ጦርነትና የግል ፍላጎትን በመተው በክልሎች ላይ ያለውን ሽኩቻ ለማስቀረትና ሰላምን ለማምጣት ሊሰራ ይገባል ሲሉም አጽኖት ሰጥተዋል፡፡
በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሰረት ሁለቱም ወገኖች በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ዜጎች ጥያቄያቸዉ እንዲመለስ ማድረግ እንደሚገባቸዉ በአፍሪካ ሕብረት መድረክ በቀረበው ሪፖርት መገለጹ የሚታወቅ ነው።
ምላሽ ይስጡ