ህፃናት ላይ የሚከሰተውን ፖሊዮ እና ተጓዳኝ በሽታዎችን ለመቀነስ ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ከየካቲት 14 እስስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የፖሊዮ ክትባት በዘመቻ ሲሰጥ መቆየቱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጿል፡፡
ለ4 ቀናት በ10 ክልሎች በተሰጠው ክትባት ከ13 ሚለየን በላይ ህጻናት መከተባቸውን በኢንስቲትዩት የፖሊዮ ወረርሽኝ ምላሽ አስተባባሪ አቶ ሚኪያስ አላዩ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልፀዋል፡፡
የክትባት ዘመቻው ለ4 ቀናት ተብሎ ቢጀመርም በአንዳንድ አካባቢዎች ዘግይተው የጀመሩ በመኖራቸው ክትባቱ እንዲቀጥል ተጨማሪ ቀናት መሰጠቱን እንዲሁም እንደ የአከባቢዎቹ ሁኔታ እየታየ ቀኑ እንደሚጨመር አብራርተዋል፡፡
ክትባቱ ከሚሰጡባቸው ክልሎች መካከል ትግራይ ላይ የነዳጅ እጥረት መኖሩ ተግዳሮት ቢሆንም በሌሎች አማራጮች ክትባቱ እንዲሰጥ መደረጉን እና በሌሎች አካባቢዎች ላይ ግን ምንም አይነት ችግር እንዳላጋጠመ ገልፀዋል፡፡
የሁለተኛውን ዙር የፖሊዮ ክትባት ሚያዚያ አጋማሽ ላይ ለመስጠት መታቀዱን በኢንስቲትዩቱ የፖሊዮ ወረርሽኝ ምላሽ አስተባባሪ አቶ ሚኪያስ አላዩ ገልፀዋል፡፡
ከውጭ ሀገራት የሚገቡት ክትባቶች እና ሌሎችም አስፈላጊ ግብዓቶች ቀደም ብለው መግባት ከቻሉ ከሚያዚያ በፊት መስጠት የሚቻል ቢሆንም ወደ ተለያዩ አከባቢዎች እስኪሰራጭ ከሚወስደው ጊዜ አንፃር በሚያዚያ አጋማሽ ለመስጠት መታቀዱን አብራርተዋል፡፡
የፖሊዮ ስርጭት በአለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአፍሪካ ስጋት የደቀነ በመሆኑ ለክትባቱ የቀናት ጭማሪ የተደረገው አንድም ህፃን በዚህ በሽታ እንዳይጠቃ ለማስቻል መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ