የተለያዩ የአዉሮፓ ሀገራት አምባሳደሮች የኢትዮጵያ መንግስት ለስደተኞች እያደረገ ያለዉን ድጋፍ ለመጎብኘት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ገልጿል፡፡
በዚህ ወቅትም ባለድርሻ አካላት በቂ እና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን የጋምቤላ ክልል በርካታ ስደተኞችን ማስጠለሉ የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልጸዉ፤ የስደተኞች ቁጥር እና የሚቀርበው የእርዳታ መጠን የማይመጣጠን በመሆኑ ባለድርሻ አካላት በቂና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ ያሳየችው ቁርጠኝነት የሚደነቅና ሊደገፍ የሚገባው መሆኑን የካናዳ፣ ጀርመን፣ ኦስትሪያ፣ ቤልጅየም፣ ኖርዌይ፣ ፊንላንድ እና ሉክዘምበርግ አምባሳደሮች ተናግረዋል ተብሏል፡፡ ልዑክ ቡድኑ ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ዜጎችን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ስደተኞች በሠላም እንዲኖሩ እየተወጣች ያለውን ኃላፊነት በበጎ መልኩ መመልከቱን አገልግሎቱ ገልጿል፡፡
መንግሥታቸው በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኛ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር የገለጹት አምባሳደሮቹ፣ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዉ ከዚህ አንጻር አምባሳደሮቹ በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ያደረጉት ጉብኝት የድጋፉን አስፈላጊነት ለመገንዘብ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
በጋምቤላ ክልል የስደተኞች አያያዝ እና የሚቀርብላቸውን ድጋፍ ለመጎብኘት አምባሳደሮቹ ወደ ስፍራው ማቅናታቸውን ያረጋገጡት በጋምቤላ ቅርንጫፍ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መዝገብወርቅ ገ/ማርያም በክልሉ ከ380 ሺ በላይ ስደተኞች እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ክልሉ ለበርካታ ስደተኞች ከለላ ከመስጠት ባለፈ ያለውን ውስን ኃብት በማጋራት ጭምር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ