በአፋር ክልል ፈንታሌ ባልተለመደ መልኩ እየወጣ ያለው ሚቴን ጋዝ ከእሳተ ጎመራ ጋር ሊያያዝ ብሎም በአከባቢው የአየር ፀባይ ላይ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል እየተገለጸ ነው።
የጋዙ መጠን እየጨመረ የሚቀጥል ከሆነ ለሰው ልጆች፤ ለእንስሳት ብሎም ለእፅዋት ጎጂ ስለሚሆን በጥናት በመመስረት በአከባቢው እና ማህበረሰቡ ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ገምግሞ የቅድመ ጥንቃቄ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነ-ምድር መምህሩ ፕሮፌሰር ጤናዓለም አየነው ገልጸዋል።
መናኸሪያ ሬዲዮ ያነጋገራቸው የአዋሽ ፈንታሌ ገቢረሱ ዞን ምክትል አስተዳደሪ አቶ ሙሳ አህመድ መረጃው አስቀድሞ እንደደረሳቸው እና ከዞኑ እና ከዱለሳ ወረዳ 9 ቀበሌዎች ለአደጋ ተጋላጭ ናቸው ተብለው የተለዩ 60ሺህ የሚጠጉ የአካባቢው ነዋሪዎች እና እንስሳቶች በክልሉ በሚገኙ 3 የአይ.ሲ.ቲ ካምፖች እንዲጠለሉ መደረጉን አስታውቀዋል።
ወደ ጊዜያዊ መጠለያ ካምፑ ለገቡ ዜጎች የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፤ ባለሀብቶች እና የተለያዩ ተቋማት የመሠረታዊ ፍጆታ እርዳታ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሁንም ከአካባቢው ያልተነሱ ነዋሪዎች መኖራቸውን ያስታወቁት ኃላፊው፤ ሁሉንም ተጋላጮች ወደ ካንፑ ለማስገባት ተግዳሮት የፈጠረውን የግንዛቤ ክፍተት ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን የአዋሽ ፈንታሌ ገቢረሱ ዞን ምክትል አስተዳዳሪው አመላክተዋል።
ማዕድን ሚኒስቴር በበኩሉ ሀገራዊ ኮሚቴ በማዋቀር የጋዙን ምንነት፣ በቀን ምን ያህል እንደሚወጣ እና ቀጣይነቱን ለማጥናት ቦታው ድረስ የባለሙያዎች ቡድን መላኩን ማስታወቁ ይታወሳል።
ምላሽ ይስጡ