በቡና መገኛነቷ በአለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ምርቷን በአለም ገበያ በጥሬው በመላክ በገበያው ተወዳዳሪ መሆኗ ይታወቃል፡፡
ምርቱን እሴትን ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለመላክ እንዲሁም የቡና ቱሪዝምን ለማሳደግ አትኮፍ ቴስት ትሬዲንግ የተባለ የግል ድርጅት በይፋ ስራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ በሀገር ውስጥ ለዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች፣ ለተለያዩ አየር መንገዶች እና ደረጃቸውን ለጠበቁ ባለ-ኮኮብ ሆቴሎች ምርቱን እንደሚያቀርብ ገልጿል፡፡
በቀጥታ ማሽን ውስጥ በማስገባት መጠቀም የሚቻል ተቆልቶ የተፈጨ ደረጃውን የጠበቀ ቡናን ለውጭ ገበያ በመላክ ሀገሪቱ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችል ስራ መጀመሩን ያስታወቁት የኢትኮፍ ቴስት ትሬዲንግ ኃላፊ አቅሌሲያ ሰለሞን ናቸው፡፡
አዲስ አበባ ላይ የተከፈተው ማዕከል ለተጠቃሚዎቹ ስለቡና ታሪክ እንዲሁም ባህላዊ ስነ-ስርዓቱን ማሳየት የሚያስችል በመሆኑ ለከተማዋ ተጨማሪ መስህብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መሰል የቡና ማዕከላት መከፈታቸው ለሀገሪቱ ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ እንደሚሆኑ የገለጹት ደግሞ የቱሪዝም ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር እንደገና አበበ ናቸው፡፡
ከዚህ ቀደም ጎብኝዎችን ቡና አብቃይ ወደሆኑ አካባቢዎች በመውሰድ የማስጎብኘት ስራ ሲሰራ እንደነበር በመግለጽ እንደ ኢትኮፍ ያሉ ማዕከላት መከፈታቸው የባህላዊ ቡና አፈላል እና አቀራረብ ስርዓቱን የሚያስተዋውቅ፤ እንዲሁም ጥራት ያለው ቡና በማቅረብ ለኢኮኖሚው አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስቴርም ቡናን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ለጀመረው እንቅስቃሴ የሚያግዝ መሆኑን በመጥቀስ፤ በዚህ ዘርፍ ለሚሰማሩ አካላት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
ኢትኮፍ ቴስት ትሬዲንግ ከሚያገኘው ትርፍ 10 በመቶ የሚሆነውን ለበጎ አድራጎት ማህበራት ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጿል፡፡
ምላሽ ይስጡ