የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በ2017 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከቀረቡለት 191 የወንጀል ጉዳዮች እና 167 ከፍታብሔር ጋር የተያያዙ የምርመራ ጥያቄዎችን ከፖሊስና ከፍርድ ቤት ተቀብሎ በፎረንሲክ ምርመራ በማጣራት 73 በመቶ ሀሰተኛ መሆናቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተለያዩ የወንጀልና የፍታብሔር ጉዳዮችን በዘመናዊ የፎረንሲክ ምርመራ ላብራቶሪ መሣሪያዎች በሚገባ እየመረመረ ውጤቱን ለሚመለከተው አካል እየሰጠ እንደሚገኝ በመግለጽ፤በፎረንሲክ ምርመራ ካደራጃቸው ዘመናዊ የላብራቶሪ ክፍሎች አንዱ የሰነድ ምርመራ ላብራቶሪ ሲሆን በሰነዶች ላይ የሚፈፀሙ ፊርማዎችን፣ በቲተሮችና በማህተሞች፣ በባንክ ቼኮች፣ በፖስፖርቶች፣ በተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ላይ የተፈፀሙ ድልዝና ስርዞችን፣ በፅሁፎች እና በቁጥሮች እንዲሁም ከውርስ ጋር የተያያዙ ሰነዶችን እና ከቦታ ካርታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በመመርመር ትክክለኛ እና ሀሰተኛ መሆናቸውን እያረጋገጠ የፍትሕ ሥርዓቱን በማገዝ የድርሻውን እያበረከተ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በሀገራችን የፀረ-ሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ሥር መንግሥታዊ እንዲሁም ሕዝባዊ ድርጅት ሰነዶችን በማስመሰል በሙሉ ወይም በከፊል የለወጠ፤ ያሻሻለ፤ የቀነሰ፤ የጨመረ ወይም በማጥፋት ወደ ሀሰተኛነት የለወጠ እንደ ወንጀሉ ክብደት እስከ እድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጎ የሚገኝ በመሆኑ ሁሉም ሊያውቀው እንደሚገባ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ምላሽ ይስጡ