በመዲናዋ የእንቁላል ዋጋ ከ17 እስከ 20 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዋጋዉ እየተጋነነ መምጣቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ የዶሮ አርቢዎች እና አቀናባሪዎች ማህበርን መናኸሪያ ሬዲዮ ጠይቋል፡፡ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ዝናው ጸሃዬ የገበያው ተለዋዋጭነት እንደተጠበቀ ሆኖ ፤በምርቱ ሂደት በኩል ከፍተኛ ተግዳሮቶች እንዳሉ አንስተዋል፡፡
የመኖ አቅርቦት ዋነኛዉ ሲሆን በአቅርቦቱ ላይ ደግሞ የተጨመረው እሴት ታክስ ሌላኛው ፈተና እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ በዚህም ከሀገር ውጪ ለማቀነባበሪያነት የሚገቡ ቫይታሚኖች ሳይቀር የዋጋ ጭማሬዎችን እያሳዩ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡አያይዘውም በአብዛኛው ጊዜ ለግብዓትነት ሊውሉ የሚችሉ ግብዓቶች በስፋት የሚገቡት የጸጥታ ችግር ባሉባቸው ክልሎች መሆኑን ተከትሎ ለዘርፉ እንቅስቃሴ አመቺ የሆኑ የትራንስፖርት አማራጮች መገኘት አለመቻላቸው ገበያውን ፈተና ውስጥ እየጣለው ስለመሆኑ አክለዋል፡፡
መናኸሪያ ሬዲዮ ከሰሞኑ በእንቁላል ዋጋ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪን በሚመለከት የቁጥጥር ስራዉን በተመለከተ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮን ጠይቋል፡፡በቢሮው የገበያ መረጃ ጥናት እና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ሙሰማ ጀማል እንደሚሉት ከሰሞኑ በእንቁላል ምርት ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሬ በሚመለከት በማህበረሰቡ በኩል የተነሱ ጥያቄዎችን ዋቢ በማድረግ እየተደረጉ ያሉ የዳሰሳ ጥናቶች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡አክለውም የግብይት ስርዓቱ ነጻ ገበያ መሆኑን ተከትሎ የዋጋ ተመን ማውጣት ባይቻልም የምርቱን ዋጋ ከሚጠበቀዉ በላይ ከፍ እንዲል ያደረጉ ምክንያቶች በመለየት የዋጋ ማረጋጋት ስራዎችን እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡
የመኖ ምርት ላይ እየታየ ያለውን የዋጋ ጭማሪ ተከትሎ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ከገበያው እንዲርቁ እያደረጋቸዉ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ